ኢየሱስ “አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ” የሆነ ገዥ
ለረጅም ጊዜ ሳታየው የቆየ አንድ ዘመድህ እንደሚመጣ አውቀህ የሚመጣበትን ጊዜ ስትጠብቅ ደስ ደስ ይልሃል። በመጨረሻም ታገኘውና ሞቅ ባለ መንገድ ሰላም ትለዋለህ። አባቱ ለምን ወደ አንተ እንደላከው ሲነግርህ በጥሞና ታዳምጠዋለህ። ከዚያም ወዲያው ወደ አገሩ የሚመለስበት ጊዜ ደረሰ። በጣም እያዘንክ ትሰናበተዋለህ። በሰላም አገሩ መድረሱን ስትሰማ እሱ በመሄዱ ምክንያት የተሰማህ ሐዘን ይቀንሳል።
ከጊዜ በኋላ የቆዩ ደብዳቤዎችን ስታገላብጥ ዘመድህ ወደ አንተ ለመምጣት ጉዞ ከመጀመሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ያከናወናቸውን ሥራዎች በአጭሩ የሚገልጹ ደብዳቤዎች ታገኛለህ። በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ የሰፈሩት ሐሳቦች ስለ እሱ የሕይወት ታሪክ አስደሳች ግንዛቤ እንድታገኝ ከማድረጋቸውም በላይ መጥቶ አንተን ስለመጠየቁም ሆነ ጠይቆህ ከተመለሰ በኋላ በማከናወን ላይ ስላለው ነገር ያለህን አድናቆት ያሳድጉልሃል።
“ከቀድሞ ጀምሮ”
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዶች ሊያገኙዋቸው ከሚችሉ ጥንታዊ ሰነዶች መካከል አንዱ የአምላክ ነቢይ የነበረው ሚክያስ ከሰባት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት የጻፋቸው ጽሑፎች ይገኙበታል። እነዚህ ጽሑፎች መሢሑ የሚወለድበትን ቦታ ይጠቁማሉ። “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፣ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፣ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” (ሚክያስ 5:2) በእነዚህ ቃላት ፍጻሜ መሰረት ኢየሱስ ቤተ ልሔም በምትባል የይሁዳ መንደር በአሁኑ አቆጣጠር 2 ከዘአበ ብለን በምንጠራው ጊዜ ተወለደ። ሆኖም አወጣጡ “ከቀድሞ ጀምሮ” ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊትም ሕልውና ነበረው። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ . . . ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው።”—ቆላስይስ 1:15፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
የጥበብ ምንጭ የሆነው ይሖዋ፣ በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የንጉሥ ሰሎሞንን አገላለጽ ከተጠቀምን፣ ‘የሥራው መጀመሪያ’ አድርጎ የፈጠረው የበኩር ልጁን ነው። ኢየሱስ ለጥቂት ጊዜያት በምድር ላይ ቆይቶ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ “በእግዚአብሔርም ፍጥረት የመጀመሪያ የነበረው” እርግጥም እሱ መሆኑን አስመስክሯል። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በጥበብ ተመስሎ ሲናገር “[ይሖዋ] ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ” ብሏል።—ምሳሌ 8:22, 23, 27፤ ራእይ 3:14
የአምላክ ልጅ ገና ከመጀመሪያው “ዋና ሠራተኛ” በመሆን አባቱን የማገዝ ልዩ የሥራ ምድብ ተቀብሏል። ይህ ይሖዋን ምንኛ አስደስቶት ይሆን! ምሳሌ 8:30 “ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፣” ካለ በኋላ አክሎ “በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ” በማለት ይገልጻል።
ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የበኩር ልጁ ሰውን በመፍጠር ሥራ እንዲሳተፍ ግብዣ አቅርቦለታል። ይሖዋ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:26) ከዚህም የተነሳ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ሌላ ነገር ተገኘ። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 8:31) ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ መክፈቻ ላይ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በፍጥረት ሥራ ውስጥ ያበረከተው ድርሻ እንደነበረ ሲያረጋግጥ “ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” ብሏል።—ዮሐንስ 1:3
የይሖዋ ቃል አቀባይ
ዮሐንስ የጻፋቸው ቃላት የአምላክ ልጅ ያገኘውን ሌላ ተጨማሪ መብት ይኸውም ቃል አቀባይ ሆኖ ማገልገሉን እንድናስተውል ያደርጋሉ። ከመጀመሪያ ጀምሮ ቃል ሆኖ አገልግሏል። ከዚህም የተነሳ ይሖዋ አዳምን ሲያነጋግረውና በኋላም አዳምንና ሔዋንን በአንድ ላይ ሲያነጋግራቸው በቃል ተጠቅሞ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። አምላክ ለሰዎች ደህንነት በማሰብ የሚሰጠውን መመሪያ በማስተላለፍ ረገድ ለሰው ዘር ፍቅር ካለው አካል ሌላ ማን የተሻለ ሆኖ ሊገኝ ይችላል?—ዮሐንስ 1:1, 2
ቃል፣ በመጀመሪያ ሔዋን ቀጥሎም አዳም በፈጣሪያቸው ላይ ሲያምፁ ሲመለከት ምን ያህል አዝኖ ይሆን! በተጨማሪም የእነሱ አለመታዘዝ በዘሮቻቸው ላይ ያመጣውን ቀውስ ለማስወገድ ምን ያህል ጓጉቶ ይሆን! (ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:6, 8፤ ሮሜ 5:12) ይሖዋ፣ ሔዋን እንድታምፅ የገፋፋትን መልአክ ማለትም ሰይጣንን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ።” (ዘፍጥረት 3:15) ቃል በኤደን ለተከሰተው ነገር የዓይን ምሥክር ከመሆኑም በላይ የሴቲቱ “ዘር” ዋነኛ ክፍል ስለሆነ ለከፋ ጥላቻ ዒላማ አንደሚሆን ተገንዝቧል። ሰይጣን ነፍሰ ገዳይ መሆኑን ያውቃል።—ዮሐንስ 8:44
ከጊዜ በኋላ ሰይጣን የታማኙን ኢዮብ ንጹሕ አቋም አጠያያቂ ባደረገ ጊዜ ቃል በአባቱ ላይ በተከመረው ስም የማጥፋት ክስ በጣም ተቆጥቶ መሆን አለበት። (ኢዮብ 1:6-10፤ 2:1-4) ቃል የመላእክት አለቃ በመሆን በሚጫወተው ሚና የተነሳ ሚካኤል ተብሎ የተጠራ ሲሆን ትርጉሙም “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ነው። ይህ ደግሞ የአምላክን ሉዓላዊነት ለመንጠቅ የሚቋምጡትን ሁሉ በመቋቋም ለይሖዋ እንዴት እንደሚቆም ያሳያል።—ዳንኤል 12:1፤ ራእይ 12:7-10
የእስራኤላውያን ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየው ሰይጣን ሰዎችን ከቅዱስ አምልኮ ለማራቅ ያደረገውን ጥረት ቃል አንድ በአንድ ይከታተል ነበር። ከግብጽ ከወጡ በኋላ አምላክ እስራኤላውያንን በሙሴ አማካኝነት እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፣ እነሆ፣ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። በፊቱ ተጠንቀቁ፣ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።” (ዘጸአት 23:20, 21) ይህ መልአክ ማን ነበር? ኢየሱስ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። ይህም ሰው ከመሆኑ በፊት ማለት ነው።
በታማኝነት መገዛት
ሙሴ በ1473 ከዘአበ ሞተና አስከሬኑ “በቤተ ፌጎር ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር” ተቀበረ። (ዘዳግም 34:5, 6) ሰይጣን የጣዖት አምልኮን ለማስፋፋት ሳይሆን አይቀርም በአስከሬኑ ለመጠቀም የፈለገ ይመስላል። ሚካኤል ይህን የተቃወመ ቢሆንም ጉዳዩን በታዛዥነት ለአባቱ ሥልጣን ለይሖዋ አስተላልፏል። ሚካኤል ‘በሰይጣን ላይ የስድብን ፍርድ ለመናገር ሳይደፍር’ “ጌታ ይገሥጽህ” በማለት ሰይጣንን አስጠንቅቆታል።—ይሁዳ 9
ከዚያም እስራኤላውያን በከነዓን የምትገኘውን የተስፋይቱን ምድር ድል እያደረጉ መያዝ ጀመሩ። ቃል የእስራኤልን ብሔር በበላይነት መምራቱን እንደሚቀጥል ኢያሱ በኢያሪኮ ከተማ አቅራቢያ በድጋሚ ማረጋገጫ አግኝቷል። ኢያሱ እዚህ ቦታ የተመዘዘ ሰይፍ ከያዘ ሰው ጋር ተገናኘ። ኢያሱ ወደ እንግዳው ሰው ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን?” ሲል ጠየቀው። እንግዳው ማንነቱን እንዲህ በማለት ሲገልጽ ኢያሱ ምን ያህል እንደተገረመ ገምት:- “አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ።” ኢያሱ ከፍ ያለ ሥልጣን ባለው በዚህ የይሖዋ ወኪል ፊት በግንባሩ መደፋቱ ምንም አያስገርምም። ይህ ግለሰብ በኋላ “አለቃው . . . መሢሕ” የሆነው ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢያሱ 5:13-15፤ ዳንኤል 9:25
የአምላክ ነቢይ በነበረው በዳንኤል ዘመን ከሰይጣን ጋር ሌላም ግድድር ተከስቶ ነበር። በዚህ ወቅት የፋርስ አጋንንታዊ አለቃ አንድን መልአክ ለሦስት ሳምንታት ‘በተቋቋመው’ ጊዜ ሚካኤል የሥራ ጓደኛው የሆነውን መልአክ ረድቶታል። መልአኩ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እነሆም፣ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት።”—ዳንኤል 10:13, 21
ሰው ከመሆኑ በፊት እና ሰው ሆኖ የነበረው ክብር
የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በ778 ከዘአበ በሞተበት ዓመት የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ፣ ይሖዋን በታላቅ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በራእይ ተመለከተ። ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ጠየቀ። ኢሳይያስ ራሱን በፈቃደኝነት ያቀረበ ቢሆንም ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን ለሚያውጀው መልእክት ምንም ምላሽ እንደማይሰጡ ይሖዋ አስጠነቀቀው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ከሃዲ አይሁዳውያን በኢሳይያስ ዘመን ከነበሩት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ “ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ” በማለት ገልጿል። ያየው የማንን ክብር ነበር? የይሖዋንና ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማያዊው ችሎት ከአባቱ ጎን ሆኖ የነበረውን ክብር ነው።—ኢሳይያስ 6:1, 8-10፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ዮሐንስ 12:37-41
ከተወሰኑ መቶ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ ከዚያ በፊት ከተቀበለው ሁሉ የሚበልጥ ሥራ ተሰጠው። ይሖዋ የሚወደው ልጁን የሕይወት ኃይል ከሰማይ ወደ ማርያም ማሕፀን አዛወረው። ከዘጠኝ ወር በኋላ ማርያም ኢየሱስን ወለደች። (ሉቃስ 2:1-7, 21) እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አገላለጽ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ።” (ገላትያ 4:4) በተመሳሳይ መንገድ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ሲያረጋግጥ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ብሏል።—ዮሐንስ 1:14
መሢሑ ተገለጠ
ወጣቱ ኢየሱስ ገና በ12 ዓመት ዕድሜው የሰማያዊ አባቱን ሥራ በመሥራት ራሱን ማስጠመድ እንደሚኖርበት ተገንዝቦ ነበር። (ሉቃስ 2:48, 49) ኢየሱስ ከ18 ዓመታት በኋላ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ በመሄድ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ኢየሱስ በመጸለይ ላይ እንዳለ ሰማያት ተከፈቱና መንፈስ ቅዱስ ወረደበት። ከአባቱ ጎን ሆኖ ቁጥር ስፍር ለሌላቸው ዓመታት በዋና ሠራተኛነት፣ በቃል አቀባይነት፣ የአምላክ ሠራዊት አለቃ በመሆንና ሚካኤል በሚል ስያሜ በሊቀ መላእክነት ያገለገለባቸውን ጊዜያት ሲያስታውስ ወደ አእምሮው የጎረፈውን ከፍተኛ ትዝታ አስብ። ቀጥሎም ለመጥምቁ ዮሐንስ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ አባቱ ሲናገር ድምፁን መስማቱ አስደስቶታል።—ማቴዎስ 3:16, 17፤ ሉቃስ 3:21, 22
መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ሕልውና እንደነበረው በፍጹም አልተጠራጠረም። ኢየሱስ ለመጠመቅ ወደ እሱ ሲመጣ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” አክሎ ሲናገርም:- “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፣ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 1:15, 29, 30፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሐዋርያው ዮሐንስም ስለ ኢየሱስ የቀድሞ ሕልውና ያውቅ ነበር። “ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል” ሲል ጽፏል።—ዮሐንስ 3:31, 32፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ሐዋርያው ጳውሎስ በ61 እዘአ ገደማ የዕብራውያን ክርስቲያኖች የመሢሑን ወደ ምድር መምጣትና ሊቀ ካህን ሆኖ የሚያከናውነውን ሥራ ጠቀሜታ እንዲያደንቁ አሳስቧቸዋል። ኢየሱስ ቃል አቀባይ በመሆን ባከናወነው ሥራ ላይ ትኩረት በመስጠት ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር . . . ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን።” ይህ የሚያመለክተው ኢየሱስ “ዋና ሠራተኛ” በመሆን በፍጥረት ሥራ የነበረውን የሥራ ድርሻም ሆነ አምላክ ሰዎችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ባደረገው ደረጃ በደረጃ የሚፈጸም ዝግጅት ውስጥ የነበረውን ተሳትፎ፣ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ሕልውና እንደነበረው ተጨማሪ ምሥክርነት መስጠቱ ነው።—ዕብራውያን 1:1-6፤ 2:9
“ከቀድሞ ጀምሮ” ታማኝ መሆን
በፊልጵስዩስ ለነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጳውሎስ የሚከተለውን ምክር ጽፎላቸዋል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:5-8) ከሞት በማስነሳትና ወደ ሰማይ እንዲመለስ በማድረግ ኢየሱስ ላሳየው ታማኝነት ይሖዋ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ሰጥቷል። ኢየሱስ በውል ለማይታወቅ ረዥም ዘመን ፍጹም አቋም ጠባቂ በመሆኑ እንዴት ያለ አስደናቂ ምሳሌ ትቶልናል!—1 ጴጥሮስ 2:21
ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕልውና መጽሐፍ ቅዱስ ለሚፈነጥቅልን የብርሃን ብልጭታዎች እጅግ አመስጋኞች ነን! እነዚህ የብርሃን ብልጭታዎች ኢየሱስ በታማኝነት በማገልገል ረገድ የተወልንን ምሳሌ ለመኮረጅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠናክሩልን ናቸው፤ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መሢሐዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ መሆኑን ስናውቅ ይህን ለማድረግ እንገፋፋለን። “አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ” የሆነውን “የሰላሙ ገዥ” ኢየሱስ ክርስቶስን እናወድሰው!—ኢሳይያስ 9:6 NW፤ ሚክያስ 5:2
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሰው ከመሆኑ በፊት ሕልውና እንደነበረው የሚያሳይ ማስረጃ
ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው ቀጥሎ የተዘረዘሩት ቃላት ሰው ከመሆኑም በፊት ሕልውና እንደነበረው በበቂ መጠን ያረጋግጣሉ:-
◻ “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፣ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።”—ዮሐንስ 3:13
◻ “እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነው . . . ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።”—ዮሐንስ 6:32, 33, 38
◻ “ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል።”—ዮሐንስ 6:50, 51
◻ “እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?”—ዮሐንስ 6:62
◻ “ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ . . . እናንተ ከታች ናችሁ፣ እኔ ከላይ ነኝ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፣ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።”—ዮሐንስ 8:14, 23
◻ “እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና።”—ዮሐንስ 8:42
◻ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።”—ዮሐንስ 8:58
◻ “አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ። አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።”—ዮሐንስ 17:5, 24
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢያሱ የይሖዋን ሠራዊት አለቃ ሲገናኝ