አንደኛ ዜና መዋዕል
20 በዓመቱ መባቻ፣* ነገሥታት ለውጊያ በሚዘምቱበት ወቅት ኢዮዓብ+ የጦር ሠራዊቱን በመምራት የአሞናውያንን ምድር አወደመ፤ ወደ ራባ+ ሄዶም ከበባት፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።+ ኢዮዓብም በራባ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ አፈራረሳት።+ 2 ከዚያም ዳዊት የማልካምን* ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱም ክብደት አንድ ታላንት* ወርቅ ነበር፤ በላዩም ላይ የከበሩ ድንጋዮች ነበሩ፤ ዘውዱም በዳዊት ራስ ላይ ተደረገ። በተጨማሪም ከከተማዋ በጣም ብዙ ምርኮ ወሰደ።+ 3 ነዋሪዎቿንም አውጥቶ ድንጋይ እንዲቆርጡ፣ ስለት ባላቸው የብረት መሣሪያዎችና በመጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው።+ ዳዊት በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። በመጨረሻም ዳዊትና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
4 ከዚህ በኋላ ከፍልስጤማውያን ጋር በጌዜር ጦርነት ተከፈተ። በዚህ ጊዜ ሁሻዊው ሲበካይ+ የረፋይም+ ዘር የሆነውን ሲፓይን* ገደለው፤ ፍልስጤማውያንም ድል ተመቱ።
5 ዳግመኛም ከፍልስጤማውያን ጋር ጦርነት ተካሄደ፤ የያኢር ልጅ ኤልሃናን የሸማኔ መጠቅለያ+ የሚመስል ዘንግ ያለው ጦር ይዞ የነበረውን የጎልያድን+ ወንድም ጌታዊውን ላህሚን ገደለው።
6 እንደገናም በጌት+ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ በዚያም በእጆቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች በእግሮቹም ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች፣ በድምሩ 24 ጣቶች ያሉት በጣም ግዙፍ የሆነ ሰው ነበር፤+ እሱም የረፋይም ዘር+ ነበር። 7 ይህ ሰው እስራኤልን ይገዳደር+ ስለነበር የዳዊት ወንድም የሺምአ+ ልጅ ዮናታን ገደለው።
8 እነዚህ በጌት+ የሚኖሩ የረፋይም+ ዘሮች ነበሩ፤ እነሱም በዳዊት እጅና በአገልጋዮቹ እጅ ወደቁ።