ሁለተኛ ዜና መዋዕል
27 ኢዮዓታም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻህ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።+ 2 ኢዮዓታም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤+ ይሁንና ሥርዓቱን ጥሶ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አልገባም።+ ሕዝቡ ግን ክፉ ድርጊት መፈጸሙን አልተወም ነበር። 3 እሱም የይሖዋን ቤት+ የላይኛውን በር ሠራ፤ በኦፌልም+ ቅጥር ላይ መጠነ ሰፊ የግንባታ ሥራ አከናወነ። 4 በተጨማሪም በተራራማው የይሁዳ ክልል+ ከተሞችን ሠራ፤+ በደን በተሸፈኑት ስፍራዎችም ምሽጎችንና+ ማማዎችን+ ገነባ። 5 ከአሞናውያንም ንጉሥ ጋር ተዋጋ፤+ በመጨረሻም አሸነፋቸው፤ በመሆኑም አሞናውያን በዚያ ዓመት 100 የብር ታላንት፣* 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴና 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ ሰጡት። በተጨማሪም አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት።+ 6 ኢዮዓታም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መንገዱን ስላጸና* ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።
7 የቀረው የኢዮዓታም ታሪክ፣ ያካሄዳቸው ጦርነቶችና የተከተለው መንገድ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።+ 8 እሱ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ።+ 9 በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ቀበሩት። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።+