-
ማቴዎስ 26:69-75አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
69 ጴጥሮስ ከቤት ውጭ፣ ግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት አገልጋይ ወደ እሱ መጥታ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው።+ 70 እሱ ግን “ስለ ምን እየተናገርሽ እንዳለ አላውቅም” በማለት በሁሉም ፊት ካደ። 71 ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ሲሄድ ሌላ ሴት አየችውና በዚያ ለነበሩት ሰዎች “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች።+ 72 እሱም “ሰውየውን አላውቀውም!” ብሎ በመማል ዳግመኛ ካደ። 73 ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአካባቢው ቆመው የነበሩት መጥተው ጴጥሮስን “አነጋገርህ* ያስታውቃል፤ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” አሉት። 74 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም!” በማለት ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። 75 ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ”+ ሲል ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። ከዚያም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
-
-
ሉቃስ 22:55-62አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
55 በግቢው መካከል እሳት አንድደው አንድ ላይ ተቀምጠው ሳለ ጴጥሮስም ከእነሱ ጋር ተቀመጠ።+ 56 ይሁንና አንዲት አገልጋይ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ ሲሞቅ አየችውና ትኩር ብላ ከተመለከተችው በኋላ “ይህ ሰውም ከእሱ ጋር ነበር” አለች። 57 እሱ ግን “አንቺ ሴት፣ እኔ አላውቀውም” ሲል ካደ። 58 ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሌላ ሰው አየውና “አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው፣ አይደለሁም” አለ።+ 59 አንድ ሰዓት ያህል ካለፈ በኋላ ደግሞ አንድ ሌላ ሰው “ይህ ሰው፣ የገሊላ ሰው ስለሆነ በእርግጥ ከእሱ ጋር ነበር!” በማለት አጥብቆ ይናገር ጀመር። 60 ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው፣ ምን እንደምታወራ አላውቅም” አለ። ገና እየተናገረም ሳለ ዶሮ ጮኸ። 61 በዚህ ጊዜ ጌታ ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል አስታወሰ።+ 62 ከዚያም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
-