-
ማርቆስ 9:19-27አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
19 እሱም መልሶ “እምነት የለሽ ትውልድ ሆይ፣+ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።+ 20 ልጁንም ወደ እሱ አመጡት፤ ልጁን የያዘው መንፈስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ወዲያውኑ ልጁን አንዘፈዘፈው። ልጁም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ አፉ አረፋ እየደፈቀ ይንከባለል ጀመር። 21 ከዚያም ኢየሱስ አባትየውን “እንዲህ ማድረግ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለው፦ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22 ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥና ውኃ ውስጥ ይጥለዋል። ማድረግ የምትችለው ነገር ካለ እዘንልንና እርዳን።” 23 ኢየሱስም “‘የምትችለው ነገር ካለ’ አልክ? እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለው።+ 24 ወዲያውም የልጁ አባት “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!”+ በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።
25 ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እነሱ ግር ብሎ እየሮጠ በመምጣት ላይ መሆኑን ሲያይ ርኩሱን መንፈስ “አንተ ዱዳና ደንቆሮ የምታደርግ መንፈስ ከእሱ ውጣ፤ ዳግመኛም ወደ እሱ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ሲል ገሠጸው።+ 26 ርኩሱ መንፈስ በኃይል ከጮኸና ብዙ ካንዘፈዘፈው በኋላ ወጣ፤ ልጁም የሞተ ያህል ሆነ፤ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “ሞቷል!” ይሉ ጀመር። 27 ይሁን እንጂ ኢየሱስ እጁን ይዞ አስነሳው፤ ልጁም ተነስቶ ቆመ።
-