-
ዮሐንስ 2:1-11አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
2 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ በምትገኘው በቃና የሠርግ ድግስ ነበር፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። 2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር።
3 የወይን ጠጁ እያለቀ ሲሄድ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው። 4 ኢየሱስ ግን “አንቺ ሴት፣ ይህ ጉዳይ እኔንና አንቺን ምን ይመለከተናል?* ሰዓቴ ገና አልደረሰም” አላት። 5 እናቱም በዚያ የሚያገለግሉትን ሰዎች “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። 6 የአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት በሚያዘው መሠረት+ እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት የፈሳሽ መለኪያዎች* የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት የውኃ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር። 7 ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው” አላቸው። እነሱም እስከ አፋቸው ድረስ ሞሏቸው። 8 ከዚያም “አሁን ቀድታችሁ ለድግሱ አሳዳሪ ስጡት” አላቸው። እነሱም ወስደው ሰጡት። 9 የድግሱ አሳዳሪም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውኃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ 10 እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ በቅድሚያ ጥሩውን የወይን ጠጅ ያቀርብና ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል።” 11 ኢየሱስ ከምልክቶቹ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ተአምር በገሊላ በምትገኘው በቃና ፈጸመ፤ ክብሩንም ገለጠ፤+ ደቀ መዛሙርቱም በእሱ አመኑ።
-