አንደኛ ዜና መዋዕል
14 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ ለዳዊት ቤት* እንዲሠሩለት መልእክተኞችን እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና* አናጺዎችን ላከ።+ 2 ዳዊትም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው አወቀ፤+ ምክንያቱም አምላክ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ሲል ንግሥናውን ከፍ ከፍ አድርጎለት ነበር።+
3 ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤+ ደግሞም ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።+ 4 በኢየሩሳሌም ሳለ የተወለዱለት ልጆች ስም ይህ ነው፦+ ሻሙአ፣ ሾባብ፣ ናታን፣+ ሰለሞን፣+ 5 ይብሃር፣ ኤሊሹዓ፣ ኤልፔሌት፣ 6 ኖጋ፣ ኔፌግ፣ ያፊአ፣ 7 ኤሊሻማ፣ ቤኤልያዳ እና ኤሊፌሌት።
8 ፍልስጤማውያንም በሙሉ ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን+ ሲሰሙ እሱን ፍለጋ ወጡ።+ ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ሊገጥማቸው ወጣ። 9 ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው በረፋይም ሸለቆ* ወረራ አካሄዱ።+ 10 ዳዊትም “ወጥቼ ፍልስጤማውያንን ልግጠም? በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ?” ሲል አምላክን ጠየቀ። ይሖዋም “አዎ ውጣ፤ እኔም በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” አለው።+ 11 በመሆኑም ዳዊት ወደ በዓልጰራጺም+ ወጥቶ በዚያ መታቸው። ከዚያም ዳዊት “እውነተኛው አምላክ፣ ውኃ እንደጣሰው ግድብ ጠላቶቼን በእጄ ደረማመሳቸው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያን ቦታ በዓልጰራጺም* ብለው ጠሩት። 12 ፍልስጤማውያንም አማልክታቸውን በዚያ ጥለው ሸሹ፤ ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረትም በእሳት አቃጠሏቸው።+
13 ከጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን ሸለቆውን* እንደገና ወረሩ።+ 14 ዳዊት ዳግመኛ አምላክን ጠየቀ፤ ሆኖም እውነተኛው አምላክ እንዲህ አለው፦ “እነሱን ለመግጠም በቀጥታ አትውጣ። ይልቁንም ከኋላቸው ዙርና በባካ* ቁጥቋጦዎቹ ፊት መጥተህ ግጠማቸው።+ 15 ደግሞም በባካ ቁጥቋጦዎቹ አናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ጥቃት ሰንዝር፤ ምክንያቱም ይህ በሚሆንበት ጊዜ እውነተኛው አምላክ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመምታት በፊትህ ወጥቷል ማለት ነው።”+ 16 ስለዚህ ዳዊት ልክ እውነተኛው አምላክ እንዳዘዘው አደረገ፤+ የፍልስጤማውያንንም ሠራዊት ከገባኦን አንስቶ እስከ ጌዜር+ ድረስ መቷቸው። 17 የዳዊትም ዝና በአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ ይሖዋም ብሔራት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ።+