ምድርን የሚወርሷት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ‘የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ’ በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ከብዙ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ መዝሙራዊው ዳዊት ‘ገሮች ምድርን ይወርሳሉ’ ብሎ ነበር። ስለ ይሖዋም “ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ተብሏል።—ማቴዎስ 5:5፤ መዝሙር 37:11፤ 115:16
ይሖዋ ሰውን ሲፈጥረው የምድር ገዥ አድርጎት ነበር። ‘እንዲያበጃትና እንዲጠብቃትም’ አዘዘው። (ዘፍጥረት 2:15) ከዚህ ይልቅ ግን ሰው እየበከላትና እያጠፋት ነው። በራእይ 11:18 ላይ ይህ ነገር እንደሚደርስና ሊያቆመው የሚችለውም አምላክ ብቻ እንደሆነ አስቀድሞ ተነግሯል። ‘ምድርን የሚያጠፏትን የሚያጠፋው’ አምላክ ነው። የሰው ልጅ የምድር ውበት ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሚያሰማው ጩኸት ጆሮውን ሲደፍን የገንዘብን ሹክሹክታ ግን አጣርቶ ይሰማል።—1 ጢሞቴዎስ 6:10
ዞሮ ዞሮ የተገኘው ገንዘብም ቢሆን ይባክናል። የዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ርዕሰ አንቀጽ አንድ አሳሳቢ ጥያቄ ጠይቋል። ይኸውም:-
“ታዲያ አሁን እውነተኞቹ እነማን ናቸው? ለምድራችን ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ይጨነቁ የነበሩት ሰዎች ለረዥም ዓመታት ሐሳባውያን፣ ሁከት ፈጣሪዎችና እዚህም እዚያም የሚሉ ተግባር የለሽ አፈኞች ተብለው ተቀልዶባቸዋል። የአሲድ ዝናብን፣ የኦዞን ንብርብር መሳሳትን፣ የግሪን ሀውስ ኢፌክትን ማለትም ከባቢ አየሩ በካርቦን ዳይኦክሳይድ ከመበከሉ የተነሣ የመጣውን የአየር ለውጥ ጨምሮ ‘ተግባር የለሾች’ የተባሉት ሰዎች ጭንቀቶቻቸው ሁሉ እውን ሆኑ።
“በሦስቱም መንገዶች እኛና ልጆቻችን ሐሳባቸው ተግባራዊ ነው የተባለላቸው ሰዎች ምኞታዊ አስተሳሰብ ያስከተለው ውጤት ብዙ ነገር እንድንሸከም አስገድዶናል። በዚያን ጊዜ በሚልዮን በሚቆጠር ወጪ ብቻ በማውጣት ልንወጣው እንችል የነበረው የአየር ብክለት ቁጥጥር ‘እውነተኛ’ ነው በተባለው ሐሳባቸው ተደናቅፎ ሊገመት በማይችል በቢልዮኖች የሚቆጠር ወጪ የሚያስወጣና ልንቋቋመው የማንችለው መላውን ዓለም ለከፍተኛ ጥፋት የሚዳርግ ችግር ከፊታችን ተደቅኖብናል።”
ስለነገሩ መላ መፈለግ ይችሉ የነበሩትም ሰዎች ቢሆኑ ብዙዎች መታመማቸውንና መሞታቸውን ቢያዩም ገንዘብ ላለማውጣት ነገሩን በማጓተት ቦርሳቸውን አሽገዋል። አሁንም ቢሆን የሚያደርጉት እንዲሁ ነው። “አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል እውነት እንደሆነ ስድስት ሺህ ዓመት ያስቆጠረው የሰው ልጅ ታሪክ አረጋግጧል።—ኤርምያስ 10:23
አምላክ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን መመሪያ ሰጥቶታል። “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” (መዝሙር 119:105) ይህም ደስታ ያስገኛል። “ታዳጊህ፣ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”—ኢሳይያስ 48:17, 18
ይሁን እንጂ አብዛኛው የሰው ዘር መለኮታዊ መመሪያን ለመቀበል የሚያስችል ገርነት የለውም፤ በመሆኑም የዚያን ውጤት ያጭዳል። ራሱን በራሱ ለመምራት ሲጣጣር ወደ ጥፋት የሚወስደውን መንገድ ለመከተል ይገፋፋል። ‘ወደ ሕይወት የሚወስደውን’ መንገድ የሚያገኙት ገሮች ብቻ ናቸው።—ማቴዎስ 7:13, 14
ዛሬ ሰዎች ለምንም ነገር ብቁ ሆነው አልተገኙም። በመጀመሪያ ራሳቸውን በሥነ ምግባር አቆሽሸው ቀጥሎ ምድርን ቀስ በቀስ በክለዋል። ምድርን ለመውረስ በአምላክ ፊት ብቃት ያሳጣቸውም ይህ የሥነ ምግባር ብልሹነት ነው። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ሰዎች የሥነ ምግባር ርኩሰታቸው ምድሪቱን ስለበከሏት እንዴት እንዲጠፉ እንደተደረጉ የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን ይዞልናል። ሁለቱም ሁኔታዎች በጥንት ዘመን የተፈጸሙ ታሪኮች ናቸው።