የሰላም ሕልሞች በነው የጠፉበት ጊዜ
1914 ከማንኛውም ተራ ዓመት የተለየ እንደሚሆን የጠበቁት ሰዎች በጣም ጥቂት ነበሩ። እንዲያውም ለቀጣዮቹ ዓመታት የነበረው ተስፋ ከተለመደው በላይ ብሩህ ሆኖ ታይቶ ነበር። ሳይንስ በሽታን በመከላከል በኩል ከፍተኛ መሻሻል ያደረገበት ወቅት ነበር። ስለ ጦርነትስ ምን ተብሎ ነበር? በ1991 በየካቲት ወር የታተመ ኤል ኦስርቫቶሬ ሮማኖ የተባለ የቫቲካን ጋዜጣ ሕዝቡ ከ1914 በፊት “ጦርነት በሩቅ ጊዜ የታሪክ ትዝታ ማኅደር ውስጥ እንደተቀመጠና” የሰው ልጅ በመጨረሻው “ከድንቁርና ተላቅቀው ብርሃን በበራላቸው ሰዎችና መንግሥታት አማካኝት ጦርነት በታገደበት ዘመን” እየኖረ ነው ብሎ ያምን እንደነበር ገልጿል።
ይሁን እንጂ 1914 እና ተከታዮቹ ዓመታት በራሱ ሥራ ረክቶ ለነበረው የሰው ልጅ ያልጠበቃቸውን አሰቃቂ ነገሮች የያዙ ነበሩ። ከተከሰቱት ነገሮች የመጀምሪያው የሰላም ሕልሞች በነው እንዲጠፉ ያደረገውና ታላቅ ጦርነት በመባል የሚታወቀው ከ1914–18 የተካሄደው ጦርነት ነበር። እንዲያውም ኤል ኦስርቫቶሬ ሮማኖ የተባለው ጋዜጣ ጦርነቱን “ካደረሳቸው ሌሎች ነገሮች መካከል የቀደሙት ትውልዶች ታላላቅ ሳይንቲስቶች ለሰላማዊ ዓላማ ይውላሉ ብለው አምነውባቸው የነበሩትን አዳዲስ ቴክኒካዊ ግኝቶች በማጥፋቱ ተለይቶ የሚታወቀው የዘመናዊው ታሪክ የመጀመሪያ ታላቅ እልቂት” ሲል ጠርቶታል። ጦርነቱ የሰላም መገኛው መንገድ ሳይንስ ነው የሚለውን እምነት መሳለቂያ አድርጎታል። ከዚህ ይልቅ ሳይንስ ጦርነቱ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አጠቃላይ እልቂት እንዲያስከትል ኃይል ሰጥቶታል።
ጦርነቱ ያስከተለው እልቂት ሲያበቃ ሌላ እልቂት ጀመረ። ከ1918–19 የተከሰተው ስፓኒሽ ኢንፍሉዌንዛ (የኅዳር በሽታ) ታላቁ ጦርነት ካስከተለው አስፈሪ እልቂት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ከ20 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች አሰቃቂ በሆነ መንገድ እንዲያልቁ አድርጓል። ተስፋ የመቁረጥ እርምጃዎች ተወስደው ነበር። በአንዳንድ አገሮች በሽታው እንዲዛመት ማድረግ እንደ ወንጀል ተደርጎ ይታይ እንደነበር ተገልጿል። ሰዎች ባደባባይ ስላስነጥሱ ብቻ በፖሊስ እየተያዙ ይታሰሩ ነበር። ሆኖም ይህን ማድረጉ ምንም ፋይዳ አላስገኘም። በሽታው ራሱ እስኪያልፍ ድረስ እንደ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ምንም ነገር ሳያግደው መዛመቱን ቀጠለ። መላው የከተማ ነዋሪ አለቀ። አስከሬኖች በየከተሞች ባሉት ሞተው የተገኙ ሰዎች ሬሳ ማቆያ ቤቶች ውስጥ ተቆለሉ።
1914 ከመድረሱ በፊት ይመጣል ተብሎ የተጠበቀው የለውጥ ዘመን የሰውን ልጅ መውጣት ወደማይችልበት አዘቅት አምዘግዝጎ ጣለው። የሰው ልጅ በራሱ ጥበብ ተመርኩዞ በጦርነትና በበሽታ ላይ ድልን ለመቀዳጀት የነበረው ከንቱ እምነት እንዲሁም ሰላምን ለማስፈን የነበሩት ሕልሞች በአሳዛኝ ሁኔታ ብትንትናቸው የወጣ የሐሳብ ቡቱቶዎች ሆነው ቀሩ። በዓለም ዙሪያ ሁኔታዎች እየባሱ መሄዳቸውን ሲቀጥሉ፣ ታላቅ የተባለው አንደኛው የዓለም ጦርነት እጅግ ግዙፍ በሆነው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማዕረጉን ሲገፈፍ፣ በሽታ፣ ድህነት፣ ድርቅና ዓመፅ እንደወረርሽኝ ባለ ሁኔታ መዛመታቸውን ሲቀጥሉ ታሪክ ጸሐፊዎች 1914 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ዓመት እንደነበረ ማስተዋል ጀመሩ።
ነገር ግን ከአብዛኛው የዓለም ሕዝብ አመለካከት በተለየ መንገድ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (ያኔ የይሖዋ ምስክሮች ይታወቁበት የነበረው ስም ነው) 1914 ከመድረሱ ከብዙ ጊዜ በፊት ወሳኝ ዓመት እንደሚሆን ጠብቀው ነበር። የይሖዋ ምስክሮች ከዚያ ጊዜ ወዲህ ባሉት ዓመታትም ዓለም ዛሬ ካለችበት ብልሹ ደረጃ የመውጣት ተስፋ በሌለው ሁኔታ እያዘቀጠች ስትሄድ ማየታቸው ያልጠበቁት አዲስ ነገር አልሆነባቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እነዚህን ነገሮች መከሰት እንዲጠባበቁ ረድተዋቸዋል። እንዲሁም ከአሁኑ ጊዜ ባሻገር አስደሳች የሆነ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጋሉ።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
Redrawn from artwork of Franklin Booth