ንዴት የሚያስከትለው የከፋ መዘዝ
በምትናደድበት ጊዜ ልብህ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል። በቅርብ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ አንድ ጥናት የልብ ሕሙማን እስከአሁን ድረስ የሚያናድዳቸውን ገጠመኝ መለስ ብለው እንዲያስታውሱ ሲጠየቁ የልባቸው ደም የመርጨት አቅም 5 በመቶ እንደቀነሰ ደርሶበታል። የልባቸው ደም የመርጨት አቅም የቀነሰው በዚያ ጊዜ ብቻ ቢሆንም የሚበሳጩ ሰዎች ሰላማዊ ከሆኑ ሰዎች ይልቅ ለልብ በሽታ የተጋለጡ መሆናቸውን የሚያመለክቱት ማስረጃዎች እየጨመሩ ከመሄዳቸው አንፃር ሲታይ ዶክተሮች የዚህ ጥናት ውጤት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ተገንዝበዋል።
የተካሄደውን ምርምር የመሩት ዶክተር ጌል አይረንሰን “ህሙማኑ በሚናደዱበት ጊዜ የልባቸው ደም የመርጨት አቅም አምስት በመቶ መቀነሱ ያን ያህል ከፍተኛ ባይሆንም ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ነው” በማለት ተናግረዋል። “ህሙማኑ ያስቆጣቸውን ሁኔታ በሚያስታውሱበት ጊዜ የተሰማቸው የቁጣ ስሜት ሁኔታው በተከሰተበት ጊዜ ከተሰማቸው በግማሽ እንደሚያንስ ተናግረዋል። የልባቸው ደም የመርጨት አቅም ያናደዳቸው ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ ሁኔታውን ካስታወሱበት ጊዜ በጣም በበለጠ መጠን ሳይቀንስ አይቀርም።”
ይህ ጥናት ንዴት በልብ የመሥራት አቅም ላይ ቀጥተኛ የሆነ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ያሳየ የመጀመሪያው ጥናት ነው። ምግብ፣ የሰውነት እንቅስቃሴና ከወላጆች የተወረሱ ባሕርያት የየበኩ ላቸውን ድርሻ ስለሚያበረክቱ ለልብ ህመም ብቸኛው መንስኤ ንዴት ባይሆንም ንዴት ለዚህ ህመም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመራማሪዎች ያምናሉ።
ዶክተሮች ንዴት በሰው አካል ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ከተገነዘቡ ቆይተዋል። የደም ግፊት መጨመር፣ የደም ዝውውር ቀውስ፣ የአተነፋፈስ ችግር፣ የጉበት መቆጣት፣ የሐሞት ማመንጨት ችግርና የጣፊያ መጎዳት ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም ንዴት እንደ አስም፣ የዓይን ሕመም፣ የቆዳ በሽታ፣ አለርጂና አልሰር እንዲሁም እንደ ጥርስ ህመምና የምግብ አለመፈጨት ችግር የመሰሉ የጤና ቀውሶችን እንደሚያባብስ ታውቋል።
ስለዚህ “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው” እንዲሁም “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በመከተል ከመንፈሳዊና ከማኅበራዊ ጥቅሞች ሌላ አካላዊ ጥቅሞችም ማግኘት ይቻላል። “ትዕግሥተኛ” የሚያደርገውን የ“ማስተዋል” ባሕርይ መኮትኮት እንዴት ያለ ጥበብ ነው። በእርግጥም “ትሑት [ሰላም ያለው የ1980 ትርጉም ] ልብ የሥጋ ሕይወት ነው።”—መዝሙር 37:8፤ መክብብ 7:9፤ ምሳሌ 14:29, 30