ጤናማ ኅብረተሰብ መገንባት
የኒው አፍሪካን መጽሔት ምክትል አዘጋጅ በቅርቡ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “በዛሬው ጊዜ ወደየትኛውም የአፍሪካ አገር ብትሄዱ ብዙሐኑ በጣም ከባድ በሆነ የድህነት ኑሮ ሲማቅቁ ጥቂት ባለጸጎች ግን በቅንጦት ሲንደላቀቁ ትመለከታላችሁ። . . . ከዚህ የድህነት ወጥመድ ልንላቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? ቀላሉ መፍትሔ ባለፀጎቹን ማስወገድና ሀብታቸውን መከፋፈል ነው። ይሁን እንጂ ይህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መፍትሔ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ለሁሉም ሰው ሊከፋፈል የሚችል በቂ ሀብት የለም። በሁለተኛ ደረጃ ባለፀጎቹን ብታስወግዱ ወዲያው በእግራቸው ሌሎች ባለፀጎች ይተካሉ። በሦስተኛ ደረጃ የኅብረተሰባዊነት ፍልስፍናዎችን ሥራ ላይ ለማዋል የተደረገው ሙከራ ድህነትን እኩል ከማከፋፈል በቀር ያስገኘው ፋይዳ የለም።
“በሁሉም አገሮችና በሁሉም ዘመናት የተሳካ ውጤት ያስገኘ አንድ የልማት መፍትሔ ብቻ አለ። እርሱም ግለሰቦች በእውቀትና በአስተሳሰብ እንዲያድጉ ማድረግ ነው። የኅብረተሰብ ፈጣሪዎች ሰዎች ናቸው። በደንብ የተማሩ፣ ጤናማ የሆኑ፣ አዎንታዊ አመለካከትና የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ጤናማና ብርቱ የሆነ ኅብረተሰብ መፍጠራቸው አይቀርም።”
ምክትል አዘጋጁ ለዚህ ማስረጃ የሚሆን ምሳሌ ቢፈልጉ ኖሮ የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ምሳሌ ይሆኗቸው ነበር። ምሥክሮቹ በአፍሪካ ውስጥ፣ እንዲያውም በመላው ዓለም ሰዎች የተማሩና ጤናማ የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሆኑ ለመርዳት በትጋት እየሠሩ ነው። ከበርካታ ተግባሮቻቸው አንዱ ጎልማሳ መኃይማንን መጻፍና ማንበብ እንዲችሉ ማስተማር ነው። በጽሑፎቻቸው አማካኝነት ስለ ንጽሕና አጠባበቅ፣ ጤንነትን ስለ መንከባከብ፣ ስለ ቤተሰብ ኑሮ ያስተምራሉ። ምሥክሮቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኛ፣ ትጉሕና አምራች ሠራተኞች እንዲሆኑ ከሚሰጣቸው ምክሮች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ በስብሰባዎቻቸውም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ያበረታታሉ።
በዚህም ከፍተኛ ውጤት አግኝተዋል። በመላው ዓለም አምስት ሚልዮን የሚያክሉ አባሎች የሚገኙበት ጠንካራ ኅብረተሰብ አላቸው። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ ይህን ያገኙትን ውጤት በራሳቸው ጥበብና ችሎታ እንዳገኙ አድርገው አይመለከቱም። ይህን የመሰለ መንፈሳዊ ብልጽግና ሊያገኙ የቻሉት “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” ከሚለው ሕያው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ።— ኢሳይያስ 48:17
ስለ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጣቸው ተግባራዊ ምክሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግህ በአካባቢህ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ሄደህ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግር ወይም በገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች ወደ አንዱ ጻፍ።