ማነው ወላጅ? ማነው ልጅ?
አንዲት በካሊፎርኒያ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩ ሳይኮሎጂስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወላጆች ሥልጣን እየተዳከመ መሄዱ በጣም ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጸዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በቢሮዬ ውስጥ በልጅና በወላጅ መካከል ሳይሆን በሁለት ትላልቅ ሰዎች መካከል የሚደረጉ የሚመስሉ በርካታ ውይይቶች ሲደረጉ ተመልክቻለሁ። የመኝታ ሰዓትን፣ የኪስ ገንዘብን፣ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችንና የመሳሰሉትን ሌሎች ጉዳዮችን የሚመለከቱ ድርድሮችን ጨምሮ በትላልቆቹ የንግድ ድርጅቶች መካከል ከሚደረጉ ድርድሮች የማይተናነሱ ድርድሮች ተደርገዋል። አንዳንድ ጊዜ ወላጁንና ልጁን ለመለየት አስቸጋሪ ይሆናል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆች ሚዛናዊ የሆነ ምክር ይሰጣል። በጣም ጥብቅ በመሆን ልጃቸውን እንዳያስቆጡ ወይም እንዳያሳዝኑትና ቅስሙን እንዳይሰብሩ ያስጠነቅቃል። (ቆላስይስ 3:21) በተጨማሪም ወላጆች ወደ ሌላው ጽንፍ በመሄድ ሥልጣናቸውን እርግፍ አድርገው እንዳይጥሉና ልጆቻቸውን ስድ እንዳይለቁ ያስጠነቅቃል። ምሳሌ 29:15 “ያልተቀጣ ብላቴና እናቱን ያሳፍራል” ይላል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ደግሞ “ባሪያውን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል” ይላል። (ምሳሌ 29:21) ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ አገልጋይ ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለልጆችም ይሠራል።
ልጆቻቸውን ተገቢ አመራርና ተግሣጽ የሚነፍጉ ወላጆች ውሎ አድሮ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ቤታቸው ከቁጥጥር ውጭ ይሆንባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ቢከተሉ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! እርግጥ ነው፣ ይህን መፈጸም ብዙ ጥረት ይጠይቃል። ቢሆንም የዕድሜ ልክ ጥቅም ያስገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ይላል።—ምሳሌ 22:6