የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 9/8 ገጽ 28-29
  • ውብ ሽፋሽፍት ካላቸው ወፎች ጋር ተዋወቁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ውብ ሽፋሽፍት ካላቸው ወፎች ጋር ተዋወቁ
  • ንቁ!—1998
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወፎች ከሕንፃዎች ጋር ሲጋጩ
    ንቁ!—2009
  • ልጆችን በዱር ማሳደግ
    ንቁ!—2001
ንቁ!—1998
g98 9/8 ገጽ 28-29

ውብ ሽፋሽፍት ካላቸው ወፎች ጋር ተዋወቁ

ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“ከዚህ ቀደም አይታችሁን አታውቁ ይሆናል። እኛ የወፍ ዝርያዎች ስንሆን በብዙ ሰዎች ዘንድ እርኩም (አፍሪካን ግራውንድ ሆርንቢልስ) በሚለው ስማችን እንታወቃለን።

“ማራኪ ከሆነው ውጫዊ ገጽታችን በተጨማሪ ሌሎች ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮችንም ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው መሬት ላይ ነው። አካላዊ መጠናችን የቱርክ ዶሮን የሚያክል ሲሆን ልክ እንደ ቱርክ ዶሮ ሁሉ የእኛም የመብረር ችሎታችን ውስን ነው።

“ጎምለል ጎምለል እያልን በመካከለኛውና በደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ እንዘዋወራለን። ድንገት ካገኛችሁን አንገታችን ላይ ባለው ቀይ ከረጢት፣ በዓይናችን ቆብና እንዲሁም ረዥምና ውብ በሆነው ሽፋሽፍታችን በቀላሉ ልትለዩን ትችላላችሁ!

“እኛ እርኩሞች የመራባት ሂደታችን ዘገምተኛ ሲሆን በአማካይ በየስድስት ዓመቱ አንድ ጫጩት እናሳድጋለን። የመራቢያ ወቅታችን ሲቃረብ ወንዶቹ እርኩሞች የደረቁ ቅጠላ ቅጠሎች ይሰበስቡና በጎጆዎቻችን ውስጠኛ ክፍል ይረበርቧቸዋል። ብዙውን ጊዜ ጎጆአችንን የምንሠራው በተቦረቦሩ ዛፎች ወይም በተፈለፈሉ ቋጥኞች ውስጥ ነው። ከዚያም ሴቶቹ የጣሏቸውን እንቁላሎች ለ40 ቀናት ይታቀፏቸዋል። የተቀረነው የቤተሰቡ አባላት ትላትሎችን፣ እጮችንና ሌሎች ጣፋጭ ምግቦችን በመለቃቀም እንቁላሉን የታቀፈችውን እናት ያለማቋረጥ እንመግባለን። ጫጩቶቹ ከተፈለፈሉ ከሦስት ወራት በኋላ ከጎጆዎቻቸው ወጥተው ከተቀረነው የቤተሰቡ አባላት ጋር ሲቀላቀሉ ስንመለከት ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል።

“የጉልምስና የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድብን ጊዜ ረዘም ያለ ነው። ሙሉ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ቢያንስ ስድስት ዓመታት ይፈጅብናል። እንዲያውም ከመሃከላችን አንዱ የራሱን ቤተሰብ ለመመሥረት ከዚህ የበለጠ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። እርግጥ ነው፣ ረዥም ዕድሜ (ብዙዎቻችን 30 ዓመት እንኖራለን) ለመኖር መቻላችን ዘር ለመተካት እንድንችል በቂ ጊዜ ይሰጠናል።

“ከሁኔታችን ለመመልከት እንደምትችሉት የምንኖረው በቤተሰብ መልክ ሲሆን አንድ ቤተሰብ ከስምንት የማይበልጡ አባላት ይኖሩታል። ሁሉም ሥራዎቻቸውን በኅብረት ይሠራሉ። እያንዳንዱ ቤተሰብ ረጃጅም ሣርና ዛፍ በሞላ ባቸው የአፍሪካ ምድሮች 100 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚደርስ ግዛት ይኖረዋል። በአንዳንድ ደቡባዊ የአፍሪካ ክፍሎች 70 በመቶ የሚሆነው መኖሪያችን ለግብርናና ለሰዎች መኖሪያነት ውሏል።

“የምንኖርበትን ግዛት እየተዘዋወርን እንጠብቃለን። በግዛታችን ውስጥ የምናገኛቸውን እባቦች፣ እጮች፣ ዔሊዎችና ነፍሳት የምንመገብ ሲሆን እነዚህን ለማንም ሌላው ቀርቶ ለሌሎች የእርኩም ቤተሰቦች እንኳ አናካፍልም። ግዛታችንን በሚዳፈሩት ላይ በቁጣ የምንዘምት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ የሞኝ ድርጊት እንፈጽማለን። እንዴት? የራሳችንን ምስል በመስኮት መስተዋት ውስጥ ስንመለከት ወራሪ ጠላት የመጣ ይመስለንና ወደ መስተዋቱ በፍጥነት እንሄዳለን። ረዥምና ጠንካራ በሆነው ምንቃር ተጠቅመን በመስተዋቱ ላይ የምንሰነዝረው ምት መስተዋቱን ምን ያክል እንደሚያረግፈው ልትገምቱ ትችላላችሁ። ብዙ መስተዋቶች በመሰባበራቸው ምክንያት አንዳንድ ሰዎች በመስኮቶቻቸው ላይ የሽቦ አጥር አድርገዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም በጣም አመስጋኞች ነን!

“የሚያሳዝነው ግን ሕልውናችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎች መኖራቸው ነው። አንዳንድ ሰዎች ከመኖሪያችን በግድ ያፈናቅሉናል። ሌሎች ድግሞ ተኩሰው ይገድሉናል። ብዙውን ጊዜ ገበሬዎች ቀበሮዎችንና ሌሎች አደገኛ እንስሳትን ለማስወገድ ሲሉ መርዝ ያለበት ምግብ ያስቀምጣሉ። ታዲያ እኛ ምግቡ መርዝ ያለው መሆኑን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? አንዳንድ ጊዜ ገበሬዎቹ ለእኛ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም መርዙን ይቀብሩታል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ምግባችንን የምናገኘው በረዥሙ አፋችን ቆፍረን በመሆኑ ቆፍረን የምናገኘው የተመረዘ ምግብ ለሞት ይዳርገናል።

“አንዳንድ ሰዎች እነዚህ አደጋዎች በእኛ ላይ እንዳይደርሱ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። እኛም ዘሩ እንደጠፋው ዶዶ እንደተባለው ወፍ ከምድረ ገጽ እንደማንጠፋ ተስፋ እናደርጋለን። ስለዚህ በሆነ ምክንያት ወደምንኖርበት አካባቢ መጥታችሁ ዱ-ዱ-ዱዱዱ ዱ-ዱ-ዱዱዱ የሚለውን ድምፃችንን ስትሰሙ ጎራ ብላችሁ ሳታዩን እንዳትሄዱ። ረዥሙን ሽፋሽፍታችንን እያርገበገብን ወደ እርኩም ግዛት እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በደስታ እንቀበላችኋለን።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ