‘ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ አእምሮን የሚያድስ’
በዩጎዝላቪያ የሚኖረው የ22 ዓመቱ ኢጎር ይህንን የተናገረው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በተመለከተ ባለፈው ዓመት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ነበር። እንዲህ ሲል ገልጿል:-
“የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ማንበብ ከጀመርኩ ጥቂት ወራት አልፈውኛል። አዳዲሶቹንም ሆነ የቆዩትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች (ከ1991 ጀምሮ ያሉትን) እያነበብኩ ሲሆን መጽሔቶቹን በጣም ወድጃቸዋለሁ። እንዲህ ዓይነቱ መጽሔት በዚህ ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ በእርግጥ አእምሮን የሚያድስ እንደሆነ ይሰማኛል።
“ስለ ሚስዮናውያን ያወጣችሁት ርዕስ ይበልጥ ማርኮኛል። ደብዳቤ እንድጽፍላችሁም ያነሳሳኝ ምክንያት ይኸው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የይሖዋ ምሥክር መሆን እችል እንደሆነ ለማወቅ እፈልጋለሁ። ካቶሊክ መሆኔን ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም፤ ይሁን እንጂ የእናንተ ሃይማኖት ከየትኛውም ሌላ ሃይማኖት በጣም የተሻለ እንደሆነ ይሰማኛል። በተለይ እንዲህ ለማለት የቻልኩት የአምላክን ቃል በማዳረስ ረገድ የእናንተን ያህል ጥረት የሚያደርግ ሌላ ሃይማኖት ስለሌለ ነው።
“ካቶሊክ የመሆኔ ጉዳይ እንቅፋት የማይፈጥርብኝ ከሆነ፣ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማወቅ እፈልጋለሁ። ከተሳካልኝ ቤልግሬድ ውስጥ የመጠመቅ ምኞት አለኝ። ይህ የሚቻል ከሆነ መቼ መምጣት እንዳለብኝና ለመጠመቅ ማሟላት ያለብኝ ነገር ካለ ደግሞ ምን እንደሆነ እባካችሁ ንገሩኝ። ምኞቴ የሚሳካ ካልሆነ እባካችሁ ልጠመቅ የምችልበትን ቦታና ስለዚህ ጉዳይ ማንን ማነጋገር እንዳለብኝ አሳውቁኝ።
“ከዚህ በመቀጠል አንድ ሰው ሚስዮናዊ መሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ። ከተጠመቅሁ በኋላ ወዲያውኑ ለሚስዮናዊ አገልግሎት ስልጠና መጀመር የምችል ከሆነ አሳውቁኝ። ከዚያ በፊት ለተወሰኑ ዓመታት ማገልገል አስፈላጊ ነው? . . .
“እባካችሁ ደብዳቤዬን በቁም ነገር ተመልከቱት። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማዳረስ ሚስዮናዊ መሆን ከሁሉ የተሻለው መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል።”
የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ዓላማ በእያንዳንዱ እትም ገጽ 2 ላይ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል:- “የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ጨቋኞችን በማጥፋት ምድርን ወደ ገነትነት የሚለውጥ መሆኑን በማስታወቅ ሰዎችን ሁሉ ያጽናናል።” የዚህን መጽሔት አንድ ቅጂ ለማግኘት ወይም አንድ ሰው እቤትዎ መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስጠናዎት የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ.ሣ.ቁ 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም ገጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች ወደሚቀርብዎ ይጻፉ።