የወጣቶች ጥፋተኛነት—መንስኤው ምንድን ነው?
ብዙውን ጊዜ ወጣት ጥፋተኞች የሚወጡት በኑሮ ዝቅተኛ ከሆኑ ቤተሰቦች ሲሆን “የጨዋ” ቤተሰብ ልጆች ግን በወንጀል ድርጊቶች እምብዛም አይካፈሉም በሚለው የተለመደ አባባል ትስማማለህ? አንዳንዶች በእስያ ያለው ሁኔታ ይህን አባባል የሚደግፍ መስሎ ይታያቸዋል። “ይህ ድሮ ቀረ” በማለት ኤዥያ ማጋዚን ዘግቧል። “በመላው እስያ በፖሊስ እጅ ያለው የስታትስቲክስ መረጃና የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው ጨዋ በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ይሰርቃሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፣ አደገኛ ዕፆችን ይወስዳሉ እንዲሁም ዝሙት አዳሪ ይሆናሉ።”
ለምሳሌ ያህል በጃፓን በከባድ የወንጀል ድርጊት ከተከሰሱት በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የመጡ ናቸው። በባንኮክም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። የሙሂታ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ኃላፊ የሆኑት አዲሳይ አሃፓነን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ባለፉት ጊዜያት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በአብዛኛው ወንጀል እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸው የነበረው የገንዘብ ችግር ነበር። ዛሬ እዚህ ካሉት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩና ምንም ዓይነት የገንዘብ ችግር የሌለባቸው ናቸው።”
አንዳንዶች ለዚህ ሁኔታ መከሰት ተቀጥረው የሚሠሩ እናቶችን፣ እየጨመረ ያለውን የፍቺ ቁጥርና በፍቅረ ንዋይ ላይ ያተኮረ አኗኗርን እንደ ምክንያት አድርገው ይጠቅሳሉ። በሲንጋፖር በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ወጣቶች የተቋቋመ የአንድ ተሃድሶ ማዕከል ረዳት ዲሬክተር የሆኑት ኤዲ ጄከብ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ዋነኛው ምክንያት የቤተሰቦች ሕይወት መቃወሱ ነው። ወላጆች ተፋትተው ሊሆን ይችላል፣ ወይም ቤተሰቡ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደር ይሆናል፣ ወይም ደግሞ ሁለቱም ወላጆች ተቀጥረው የሚሠሩ ይሆኑና ልጆቹ ችላ ይባላሉ። ልጆች ጥሩ ሥነ ምግባሮችን የሚማሩት ከቤት ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜያችን እየጨመረ በሚሄድ የወጣቶች ዓመፅ ተለይቶ እንደሚታወቅ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ሆኖም ይኸው መጽሐፍ ቤተሰቦች በየትኛውም የኢኮኖሚ ሁኔታ ሥር ይሁኑ ተቀራርበው መኖር የሚችሉበትን ሥነ ምግባራዊ መመሪያ ሊሰጣቸው ይችላል። “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅም በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ሊመረመር የሚገባው መጽሐፍ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በእስያም ሆነ በተቀረው የዓለም ክፍል የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ደረጃ በማጥናት ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ ናቸው። አንተም ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ትችል ዘንድ ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣት ጥፋተኛ መሆን ወይስ የአምላክን ሞገስ ማግኘት? ምርጫው የአንተ ነው