“በገነት የመኖር ሕልማችን”
ባለፈው ዓመት ፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሌ ሞሮቤ በሚባል አውራጃ ከሚኖር አንድ የንቁ! ደንበኛ ደብዳቤ ደርሶት ነበር። ደብዳቤው እንደሚከተለው ይነበባል:-
“ከአምስት ዓመታት በፊት (በሞርስቤይ ወደብ ሳለሁ) ድርጅታችሁ የሚያትመውን የንቁ! መጽሔት ለማንበብ ወስኜ ነበር። ይህን ውሳኔ ሳላደርግ ቀርቼ ቢሆን ኖሮ እንደሚቆጨኝ ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ። ከ1997 ጀምሮ የወጡትን እትሞች በሙሉ ያነበብኩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ብዙ የንቁ! መጽሔቶች አሉኝ።
“ንቁ! መጽሔትን በማንበቤ ብዙ ተምሬአለሁ። አዳዲስ ቃላት አውቄያለሁ። በጠቅላላ እውቀትና በሰዋሰው ረገድም ያለኝ እውቀት ከፍ ብሏል። ስለ ፈጣሪ ያለኝ ግንዛቤም ጨምሯል። ይበልጥ ታጋሽ፣ ለሰው አሳቢና ትጉ ሆኛለሁ። ለዕፅዋትና ለእንስሳት ያለኝ አድናቆትም ጨምሯል። ብዙ ሰዎች ንቁ! መጽሔትንና ሌሎች ጽሑፎቻችሁን እንዲያነብቡ አበረታታለሁ።”
ጸሐፊው ሲያጠቃልሉ የሚከተለውን ብለዋል:- “በዓለም ላይ ያለው እያንዳንዱ ሰው የይሖዋ ምሥክር ቢሆን ኖሮ በገነት የመኖር ሕልማችን ዛሬውኑ እውን ይሆን ነበር ብዬ አምናለሁ። በዚሁ ቀጥሉ።”
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁአቸው ጽሑፎች ይህ የአሁኑ ሥርዓት በቅርቡ ጠፍቶ በአምላክ መንግሥት በሚተዳደረው አዲስ ዓለም እንደሚተካ በሚናገረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ የሰው ልጆችን ችግር የሚያስወግደው ይህ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ይገልጻል።
እርስዎም ይህን 192 ገጽ ያለውን መጽሐፍ ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት በገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መላክ ይችላሉ።
□ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ላኩልኝ።
□ መጽሐፍ ቅዱስ መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።