“ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ!” የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
● ከግንቦት 21-23 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚደረገው ስብሰባ የሚጀምሩት በሺህ የሚቆጠሩት የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባዎች በቀጣዮቹ ወራት በመላው ዓለም ይካሄዳሉ። በኢትዮጵያ ሦስቱም ቀናት እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ የሚጀምረው ከጠዋቱ 3:20 ላይ በሚደመጥ ሙዚቃ ይሆናል። የዓርብ ዕለት ጭብጥ “ለእኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይሻለኛል” የሚል ሲሆን በመዝሙር 73:28 ላይ የተመሠረተ ነው። ከሊቀ መንበሩ ንግግር በኋላ “የአውራጃ ስብሰባዎች ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ይረዱናል” እንዲሁም “ወልድ ስለ አብ ሊገልጥልን ፈቃደኛ ነው” የሚሉት ንግግሮች ይቀርባሉ። ከዚያም “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበራቸውን ሰዎች ምሳሌ ተከተሉ” የሚል ርዕስ ባለው ሲምፖዚየም ሥር አብርሃም፣ ሩት፣ ሕዝቅያስና ማርያም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሠረቱት እንዴት እንደሆነ የሚያብራሩ ንግግሮች ይቀርባሉ። የጠዋቱ ፕሮግራም “ይሖዋ ወደ እኛ የሚቀርበው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ባለውና የስብሰባውን ጭብጥ በሚያብራራው ንግግር ይደመደማል።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የመጀመሪያው ንግግር “ይሖዋን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በመቀጠልም “በይሖዋ ተግሣጽ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ሁኑ” እና “ፈጽሞ ‘በይሖዋ ላይ አታማርሩ’” የሚሉ ንግግሮች ይቀርባሉ። በመቀጠል ደግሞ “የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ቤተሰቦች ከይሖዋ ጋር ተቀራርበው እንዲኖሩ ይረዳቸዋል” በሚል ርዕስ አምስት ንግግሮች ያሉት ሲምፖዚየም ይቀርባል። ንግግሮቹ “የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሆነው ይሖዋ፣” “ባሎች፣ ከሚስቶቻችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ፣” “ሚስቶች፣ ከባሎቻችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ፣” “ወላጆች፣ ከልጆቻችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ” እና “ልጆች፣ ከወላጆቻችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ” የሚል ርዕስ አላቸው። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የሚደመደመው “ፍጥረት ‘ሕያው የሆነውን አምላክ’ ይገልጣል!” በሚል ርዕስ በሚቀርበው ንግግር ይሆናል።
የቅዳሜው ስብሰባ ጭብጥ “ከቅኖች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አለው” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የተመሠረተውም በምሳሌ 3:32 [NW] ላይ ነው። “ሰዎች ‘ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ’ እርዷቸው” በሚል ጭብጥ የሚቀርበው አምስት ንግግሮች ያሉት ሲምፖዚየም “ከአምላክ የራቁና ተስፋ ያጡ፣” “ጥያቄ አቀረበላቸው፣” “የወንጌሉ ሰባኪ ረዳት ስትሆኑ ድርሻችሁን ተወጡ፣” “በመልካም ባሕርያችሁ ማርኳቸው፣” እና “የምታደርጉትን ጥረት በቅንዓት ቀጥሉ” የሚል ርዕስ ያላቸውን ንግግሮች ይዟል። “የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን ዝምድና ያጠናክረዋል” እንዲሁም “ይሖዋን የሚወዱ ‘ዕንቅፋትም የለባቸውም’” የሚሉ ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በጥምቀት ንግግር ይደመደማል፤ ከዚያም ብቃቱን ያሟሉ የጥምቀት ዕጩዎች ይጠመቃሉ።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው “ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ” የሚል ርዕስ ያለው ስምንት ክፍሎች ያሉት ሲምፖዚየም “የሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች፣” “ኩራት፣” “ገንዘብ፣” “ጤና፣” “ሥራ፣” “መዝናኛ፣” “ቤተሰብ” እና “ቴክኖሎጂ” የሚሉ ንግግሮችን ይዟል። ከዚያም “ይሖዋ እርማት ሲሰጣችሁ አትታክቱ!” የሚል ርዕስ ያለው በድምፅ ብቻ የሚቀርብ ልዩ ድራማ ይከተላል። የዕለቱ ፕሮግራም የሚደመደመው “ኤርምያስ እንዳደረገው ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ” በሚለው ንግግር ይሆናል።
የእሁድ ዕለት ጭብጥ “አምላካችሁን ይሖዋን አጥብቃችሁ ያዙ” የሚል ሲሆን በኢያሱ 23:8 [NW] ላይ የተመሠረተ ነው። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በመዝሙርና በጸሎት ከተከፈተ በኋላ “የይሖዋን ባሕርያት ማድነቅ” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ሲምፖዚየም “በቀላሉ የሚቀረብ፣” “የሰዎችን ስሜት የሚረዳ፣” “አድናቂ፣” “ደግ፣” “የማያዳላ፣” “ይቅር ባይ፣” “ምክንያታዊ” እና “ታማኝ” በሚሉት ንግግሮች የይሖዋን ስምንት ባሕርያት ያብራራል። ቀጥሎ ደግሞ “ወደ አምላክ መቅረብ የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚል ጭብጥ ያለው የሕዝብ ንግግር ይቀርባል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ሳምንታዊውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ፍሬ ሐሳብ በማቅረብ ይደመደማል።
የከሰዓት በኋላውን ስብሰባ ለየት የሚያደርገው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ሁኔታ የሚያሳየው ጥንታዊ አለባበስ የሚንጸባረቅበት ድራማ ነው። “በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ” የሚል ጭብጥ ያለው ይህ ድራማ ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም ሲሸሹ የነበረውን ሁኔታ ያሳያል። ከዚያም የአውራጃ ስብሰባው የሚደመደመው “ምንጊዜም ‘በልዑሉ ሚስጥራዊ ቦታ’ ኑሩ” በሚል ጭብጥ በሚቀርበው ንግግር ይሆናል።
በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሁኑኑ እቅድ ያውጡ። ስብሰባው በአቅራቢያዎ የሚካሄድበትን ቦታ ለማወቅ ከፈለጉ በአካባቢዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው መጠየቅ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ይችላሉ። የመጋቢት 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ስብሰባው በኢትዮጵያ የሚደረግባቸውን ቦታዎች ዝርዝር ይዞ ወጥቷል።