የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g17 ቁጥር 5 ገጽ 14-15
  • ካዛክስታንን እንጎብኝ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ካዛክስታንን እንጎብኝ
  • ንቁ!—2017
ንቁ!—2017
g17 ቁጥር 5 ገጽ 14-15
አስታና፣ ካዛክስታን

የአስታና ከተማ

አገሮችና ሕዝቦች | ካዛክስታን

ካዛክስታንን እንጎብኝ

የካዛክስታን ካርታ

የካዛክስታን ሕዝቦች ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ነበሩ። ዛሬም ቢሆን አንዳንድ የካዛክስታን ከብት አርቢዎች እንደየወቅቱ ከብቶቻቸውን ይዘው ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ። በጋውን የሚያሳልፉት፣ ደጋ ላይ በሚገኙት ቀዝቀዝ ያሉ የግጦሽ አካባቢዎች ነው። ከዚያም በረዶ የሚጥልበት የቅዝቃዜው ወቅት እየቀረበ ሲመጣ መንጎቻቸውን እየነዱ ሞቃት ወደሆኑት የቆላ አካባቢዎች ይወርዳሉ።

አንዳንድ የካዛክስታን ሰዎች ዘመናዊ በሆኑ ከተሞች ይኖራሉ። ያም ቢሆን ብዙዎቹ ባሕሎቻቸው፣ ምግቦቻቸውና የዕደ ጥበብ ሥራዎቻቸው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ይኖሩ የነበሩትን ቅድመ አያቶቻቸውን የአኗኗር ዘይቤ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ካዛኮች በሥነ ግጥም፣ በዘፈንና በባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በተቀናበሩ ሙዚቃዎች ረገድ ግሩም ቅርስ አላቸው።

የርት የሚባለው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል ባሕላዊ ቤት፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ከብት አርቢዎችም ለመኖሪያነት የሚመርጡት የርትን ሲሆን በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ካዛኮች ደግሞ ለልዩ ዝግጅቶች ይጠቀሙበታል። በተጨማሪም የርት ለጎብኚዎች ምቹ ማረፊያ ሆኖ ያገለግላል። የርቶች ከውስጥ በኩል በጥልፍ፣ በሽመና ሥራዎችና በስጋጃዎች ያጌጡ በመሆናቸው የካዛክስታን ሴቶችን የዕደ ጥበብ ሙያ የሚያሳዩ ቤተ መዘክሮች ናቸው ሊባል ይችላል።

የርት ውስጥ ያለ አንድ ቤተሰብ

የርት ከውስጥ ሲታይ

በገጠር አካባቢ የሚኖሩ የካዛክስታን ቤተሰቦች ለፈረሶቻቸው ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። በካዛክስታን ቋንቋ ፈረሶች የሚጠሩባቸው ቢያንስ 21 ስያሜዎች ያሉ ሲሆን እነዚህ ስያሜዎች የሚሠራባቸው ከፈረሶች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ነገሮችን ለመግለጽ ነው፤ በተጨማሪም የፈረሶችን ቀለም ለማመልከት የሚያገለግሉ ከ30 በላይ ቃላትና አገላለጾች አሉ። ዛሬም ቢሆን ጥሩ ፈረስ፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውድ ስጦታ ነው። በገጠር አካባቢ ወንድ ልጆች ከትንሽነታቸው ጀምረው ግልቢያ ይማራሉ።

በካዛክስታን ሕዝቦች ባሕላዊ ምግብ ውስጥ ምንጊዜም ቢሆን ሥጋ የሚካተት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ምግባቸውን ሲያዘጋጁ ብዙም ቅመም አይጠቀሙም። የካዛክስታን ሕዝቦች በጣም ከሚወዷቸው መጠጦች መካከል፣ ከባዝራ ወተት የሚዘጋጀውና ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሚነገርለት ኩሚስ እንዲሁም ከግመል ወተት የሚዘጋጀውና ትንሽ ኮምጠጥ የሚለው ሹባት ይገኙበታል።

በአልማቲ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለጉብኝት ክፍት ነው።

የበረዶ ነብር

በቀላሉ የማይገኘው የበረዶ ነብር የበጋውን ወራት የሚያሳልፈው በካዛክስታን ተራሮች አናት ላይ ነው

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በካዛክስታን ቢያንስ 36 የቱሊፕ አበባ ዝርያዎች ይበቅላሉ፤ በካዛክስታን ባሕላዊ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ የቱሊፕ ቅርጽ ማየት የተለመደ ነው።

ባልካሽ የተባለው የካዛክስታን ሐይቅ በምሥራቅ በኩል ውኃው ጨዋማ ሲሆን በምዕራብ በኩል ደግሞ ጨርሶ ጨው የሌለበት ነው ሊባል ይችላል።

ንስሮችንና ሌሎች አዳኝ ወፎችን አሠልጥኖ ለአደን መጠቀም በጣም የተለመደ ነው። ካዛኮች ወርቃማ ንስሮችን በጣም የሚወዷቸው ሲሆን እነሱን በማሠልጠን ረገድ ተወዳዳሪ የላቸውም።

ጭንቅላቱ ላይ መከለያ የተደረገለት ንስር በአንድ ሰው እጅ ላይ

በንስር ጭንቅላት ላይ የሚደረገው መከለያ ወፉ ሰዎችን እንዳይፈራ ይረዳዋል

  • በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎች፦ ካዛክ፣ ሩሲያኛ

  • የሕዝብ ብዛት፦ 17,563,000

  • ዋና ከተማ፦ አስታና

  • የአየር ንብረት፦ በበጋ ሞቃትና ደረቅ፣ በክረምት ቀዝቃዛና በረዷማ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ