ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፤ ለእውነት አብረው የሚደክሙ ሠራተኞች
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤዎችን ለማነጽ የሚጐበኙ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ነበሩ። በጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ለአምላክ እንደሚገባ ሆነው ለመመላለስ እንዲችሉ ለመርዳት የግል ጥቅማቸውን ሳይፈልጉ ራሳቸውን ለወንድሞቻቸው አገልግሎት ሰጥተዋል።—ሥራ 11:23, 24፤ 14:21, 22፤ 15:32፤ 20:2, 31–35፤ ፊልጵስዩስ 2:20–22, 29፤ 1 ተሰሎንቄ 2:5–12
በአሁኑ ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች የስብከት እንቅስቃሴና በበላይ ተመልካችነት ሥራ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ አካብተዋል። ራሳቸውን ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማቅረብ እንዲችሉ ራሳቸውን ከሥጋዊ ሥራና ከቤተሰብ ኃላፊነቶች ነፃ አድርገዋል። ያገቡትም ቢሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ሚስቶቻቸው ከእነርሱ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ የቆዩ ናቸው።
አንድ የክልል የበላይ ተመልካች ከ18 እስከ 25 የሚደርሱ ጉባኤዎች የሚገኙበትን ክልል እንዲያገለግል ይመደባል። በክልሉ ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ያህል ይጐበኛል። ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመት በኋላም ወደ ሌላ ክልል ይዛወራል። በዚህ መንገድ ጉባኤዎች የተለያዩ የክልል የበላይ ተመልካቾች ካሏቸው የተለያየ ተሞክሮና ችሎታ ይጠ ቀማሉ።
የክልል የበላይ ተመልካቹ የጉባኤውን መንፈሳዊ ሁኔታና እንቅስቃሴ ይመረምራል። ለጉባኤው የተለያዩ ንግግሮችን ይሰጣል። እንዲሁም ከሽማግሌዎችና ከዲያቆናት ጋር ተገናኝቶ ለጉባኤው የሚሰጡትን አገልግሎት እንዴት ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ ይነጋገራል።
በሳምንቱ ውስጥ እሱና ሚስቱ (ያገባ ከሆነ) በጉባኤው ውስጥ ካሉት ምሥክሮች ጋር አብረው በማገልገል ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉትን አገልግሎት እንዲያሻሽሉ ይረዷቸዋል። በተጨማሪም እሱና ሚስቱ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎችን በመጐብኘት በእምነት ያበረታቷቸዋል። አንተንም እንዲጐበኙህ ልትጠይቅ ትችላለህ።
የወረዳ የበላይ ተመልካቹም ተመሳሳይ የሆነ መንፈሳዊ ብቃትና የሥራ ልምድ አለው። ከክልል ስብሰባዎች ጋር የተያያዘ አገልግሎት በመስጠት በየሳምንቱ ከክልል ወደ ክልል ይጓዛል። እሱና ሚስቱ በሚጐበኙት ክልል በሚገኝ ጉባኤ ካሉ ምሥክሮች ጋር በመስክ አገልግሎት አብረው ይሠራሉ። የክልል ስብሰባውን ፕሮግራም የመጨረሻ ዝግጅት ይቆጣጠራል። በስብሰባው ወቅትም የሕዝብ ንግግሩን ጨምሮ የተለያዩ ንግግሮችን ይሰጣል።
ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በአንድ ጉባኤ ወይም ክልል የሚያደርጉትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሌላ ጉባኤ ወይም ክልል ይሄዳሉ። አንድ ዓይነት ፕሮግራም ተከትለው ሁሉንም ጉባኤዎች ወይም ክልሎች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጐብኝተው ከጨረሱ በኋላ አዲስ ዙር ይጀምራሉ።
በብዙ አገሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በራሳቸው መኪና ወይም በሕዝብ ማመላለሻ ይጓጓዛሉ። በብስክሌት ወይም በእግር የሚጓዙባቸው አገሮችም አሉ። ማኅበሩ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾቹን የመጓጓዣ ወጪ ይሸፍናል። እርሱና ሚስቱ ላወጡት መተኪያ የሚሆን መጠነኛ ገንዘብ ይሰጣቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቹና ለሚስቱ ማረፊያና ምግብ በእያንዳንዱ ጉባኤ አባሎች ይዘጋጅላቸዋል።
ይህን አገልግሎት ለመፈጸም ራስን የመሰዋት መንፈስ ያስፈልጋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው በጉባኤዎች ላይ ከባድ ሸክም ሳይጭኑ አገልግሎታቸውን ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።—1 ተሰሎንቄ 2:9
● በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የክርስቲያን ጉባኤ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን የሚጐበኙት ለምን ዓላማ ነበር?
● በአሁኑ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ለዚህ አገልግሎት ብቁ ሆነው የተገኙትና ራሳቸውን ያቀረቡት እንዴት ነው?
● የክልል እና የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን አገልግሎትና አኗኗር ግለጽ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በክልል ስብሰባ ንግግር ሲያደርግ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የክልል የበላይ ተመልካች ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው ስብከት እንዴት እንደሚከናወን ትምህርት ይሰጣል። ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ይነጋገራል። አዲስ ፍላጎት ካሳዩ ሰዎች ጋር የሚደረገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይጐበኛል፤ ለጉባኤዎች ንግግር ይሰጣል