የጀርባው ሽፋን
ቤተሰብ ከሰብዓዊ ተቋሞች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ ነው፤ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ችግር ላይ ወድቋል። አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱና የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተበራከቱ መሄዳቸው፣ ዘመናዊ መቅሰፍት የሆነው ፍቺና በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸም ዓመፅ፣ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱና ሌሎች ከባድ ችግሮች መኖራቸው አንዳንዶች የቤተሰብ ሕይወት ከቆመበት የውድቀት አፋፍ መትረፉን እንዲጠራጠሩ አድርገዋቸዋል።
ያም ሆኖ ግን የቤተሰብ ሕይወት የተረጋጋና ተስማሚ መሆን የሚችልበት መንገድ ይኖራልን? አዎ፣ የቤተሰብ አባላት የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበትን ቁልፍ ማወቅ ከቻሉ ሕይወታቸው አስደሳች የማይሆንበት ምክንያት የለም። ቁልፉ የተሰወረ ነገር አይደለም። ለብዙ፣ ብዙ መቶ ዘመናት በተግባር ተፈትኖ የታየ ነው። ታዲያ ይህ ቁልፍ ምንድን ነው? ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው ይህ መጽሐፍ መልሱን ይሰጠናል። በተጨማሪም ይህ “ቁልፍ” በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩትን የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመፍታት እንዴት ሊረዳ እንደሚችል የሚያሳዩ በእውን የተፈጸሙ ምሳሌዎችን ይዟል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ የማይፈልግ ሰው ይኖራልን?