በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት እና የኋላ ታሪካቸው ጥናት
ጥናት ቁጥር 2—ጊዜ እና ቅዱሳን መጻሕፍት
ይህ ርዕስ የመጽሐፍ ቅዱስን የጊዜ አከፋፈል፣ በጣም የተለመደውን የዘመናት አቆጣጠር፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር መነሻ ሆነው ያገለገሉትን ዓመታት፣ እንዲሁም የጊዜን ሂደት አንዳንድ ገጽታዎች ያብራራል።
የሰው ልጅ ጊዜ አላፊ መሆኑን በሚገባ ያውቃል። እያንዳንዱ ደቂቃ ባለፈ ቁጥር በጊዜ ሂደት ውስጥ አንድ እርምጃ ወደፊት ይጓዛል። ጊዜውን በሚገባ ከተጠቀመበት በእርግጥም ጥበበኛ ሆነ ማለት ነው። ንጉሥ ሰሎሞን እንደጻፈው “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወን ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፦ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ የተተከለውን ለመንቀልም ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው።” (መክ. 3:1-4) ጊዜ በፍጥነት ይነጉዳል! ለሰው የተሰጠው የ70 ዓመት ዕድሜ በጣም ሰፊ ከሆነው የእውቀት ክምችት ተጠቃሚ ለመሆንና ይሖዋ በዚህች ምድር ላይ ለሰው ልጆች መጠቀሚያ እንዲሆኑ ባዘጋጃቸው መልካም ነገሮች በሙሉ ለመደሰት የሚበቃ አይደለም። “አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ አድርጎ ሠርቶታል። ደግሞም ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል፤ ይሁንና የሰው ልጆች እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም።”—መክ. 3:11፤ መዝ. 90:10
2 ይሖዋ ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር አምላክ ነው። ፍጥረታቱንም በጊዜ ሂደት ውስጥ ቦታ እንዲያገኙ ለማድረግ መልካም ፈቃዱ ሆኗል። ዓመፀኛ የሆነው ሰይጣንን ጨምሮ የሰማይ መላእክትም የጊዜን አካሄድና አላፊነት አሳምረው ያውቃሉ። (ዳን. 10:13፤ ራእይ 12:12) ስለ ሰው ልጆችም “ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል” ተብሏል። (መክ. 9:11) አምላክን ሁልጊዜ የሚያስብና “በተገቢው ጊዜ” የሚሰጠውን መንፈሳዊ ምግብ የሚቀበል ሰው ደስተኛ ነው።—ማቴ. 24:45
3 ጊዜ የሚጓዘው በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው፦ ጊዜን የማያውቅ ሰው የሌለ ቢሆንም የጊዜን ምንነት በትክክል ሊናገር የሚችል ግን የለም። ልክ እንደ ሕዋ ሊደረስበት የማይቻል ነገር ነው። ጊዜ መቼ እንደጀመረም ይሁን ወዴት እየተጓዘ እንዳለ የሚያውቅ ማንም የለም። እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያውቀው “ከዘላለም እስከ ዘላለም አንተ አምላክ ነህ” የተባለውና ለእውቀቱ ዳርቻ የሌለው ይሖዋ ብቻ ነው።—መዝ. 90:2
4 በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜ ልንረዳ የምንችላቸው አንዳንድ ባሕርያት አሉት። የጊዜን የጉዞ ፍጥነት መለካት ይቻላል። በተጨማሪም ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንደሚያስኬድ መንገድ ለአንድ አፍታ እንኳ ቆም ሳይል ወደፊት ብቻ ይገሰግሳል። የግስጋሴው ፍጥነት ምንም ያህል ቢሆን ወደኋላ እንዲመለስ ማድረግ ፈጽሞ አይቻልም። የምንኖረው ጊዜያዊ በሆነ የአሁን ጊዜ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የአሁን ጊዜ ወደ ኋላ እየተወን ያለማቋረጥ ይጓዛል። ለአንድ አፍታ እንኳ እንዲቆም ማድረግ አይቻልም።
5 ያለፈው ጊዜ፦ ያለፈው ጊዜ ታሪክ ሆኖ ስላለፈ ፈጽሞ ሊደገም አይችልም። ያለፈውን ጊዜ እንዲመለስ ለማድረግ መሞከር ቁልቁል የሚፈስን ፏፏቴ ተመልሶ ሽቅብ እንዲወጣ ወይም የተወነጨፈን ቀስት ወዳስወነጨፈው ደጋን እንዲመለስ ለማድረግ የመሞከር ያህል ነው። ያደረግናቸው ስህተቶች በጊዜ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ትተው አልፈዋል። ይህን አሻራ ሊፍቅልን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ኢሳ. 43:25) በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ሰው ባለፉት ጊዜያት ያደረጋቸው መልካም ነገሮች በጥሩነት ተመዝግበው ይቆዩና ወደፊት የይሖዋን በረከት ያስገኙለታል። (ምሳሌ 12:14፤ 13:22) ያለፈውን ጊዜ በጥሩም ሆነ በመጥፎ መንገድ ተጠቅመንበታል። አሁን ምንም ልናደርግ የምንችለው ነገር የለም። ክፉዎችን በተመለከተ “እንደ ሣር በፍጥነት ይደርቃሉ፤ እንደለመለመ ተክልም ይጠወልጋሉ” ተብሏል።—መዝ. 37:2
6 የወደፊቱ ጊዜ፦ የወደፊቱ ጊዜ ግን ከዚህ ይለያል። ሁልጊዜ ወደ እኛ ይጓዛል። በአምላክ ቃል እርዳታ ከፊታችን የሚመጡብንን እንቅፋቶች አስቀድመን ልናውቅና እንዴት መቋቋም እንደምንችል ልንዘጋጅ እንችላለን። ‘በሰማይ ለራሳችን ሀብት’ ማከማቸት እንችላለን። (ማቴ. 6:20) ይህ ዓይነቱ ሀብት በጊዜ ሂደት ተጠርጎ አይጠፋም። ከእኛ ጋር የሚኖር ከመሆኑም በላይ ዘላቂ የሆነ ዘላለማዊ በረከት ያስገኝልናል። ጊዜያችንን በጥበብ ስለ መጠቀም አጥብቀን የምናስበውም ይህን የወደፊቱን ጊዜያችንን የሚመለከት በመሆኑ ነው።—ኤፌ. 5:15, 16
7 ጊዜ አመልካቾች፦ በዘመናችን የምንጠቀምባቸው የግድግዳና የእጅ ሰዓቶች ጊዜ አመልካቾች ናቸው። ለጊዜ መለኪያነት ያገለግሉናል። በተመሳሳይም ፈጣሪያችን ይሖዋ የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ የጊዜ አመልካቾችን አዘጋጅቷል። ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ፣ ጨረቃ ደግሞ በምድርና በፀሐይ ዙሪያ እንዲዞሩ በማድረግ የሰው ልጅ በሚኖርበት ምድር ላይ ሆኖ የጊዜን አካሄድ እንዲከታተል አስችሏል። “አምላክም እንዲህ አለ፦ ‘ቀኑና ሌሊቱ እንዲለይ በሰማያት ጠፈር ላይ ብርሃን ሰጪ አካላት ይኑሩ፤ እነሱም ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን የሚጠቁሙ ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ።’” (ዘፍ. 1:14) በዚህ መንገድ እነዚህ የጠፈር አካላት በአንድ ዓላማ እንደተሳሰሩ ያህል ፍጹም በሆነና ዝንፍ በማይል የማያቋርጥ ሂደት እየተዟዟሩ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚጓዘውን የጊዜ ፍሰት ይለኩልናል።
8 ቀን፦ “ቀን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ትርጉሞች ተሠርቶበታል። በዘመናችንም ቢሆን የተለያየ ትርጉም አለው። ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ አንድ ሙሉ ዙር ስታከናውን የ24 ሰዓት ርዝመት ያለው አንድ ሙሉ ቀን ትሰፍርልናለች። በዚህ አገባቡ አንድ ቀን የብርሃኑንና የማታውን ጊዜ የሚያጠቃልል የ24 ሰዓት ርዝመት ያለው ጊዜ ነው። (ዮሐ. 20:19) ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የ12 ሰዓት ርዝመት የሚኖረው የብርሃን ጊዜም ቀን ተብሎ ተጠርቷል። “አምላክም ብርሃኑን ‘ቀን’ ብሎ ጠራው፤ ጨለማውን ግን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው።” (ዘፍ. 1:5) ይህም አብዛኛውን ጊዜ የ12 ሰዓት ርዝመት የሚኖረውና የጨለማ ጊዜን የሚያመለክተው “ሌሊት” የተባለው ቃል እንዲኖር ምክንያት ሆኗል። (ዘፀ. 10:13) “ቀን” የሚለው ቃል አንድ ታዋቂ የሆነ ሰው በሕይወት የኖረበትን ዘመን ለማመልከትም ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢሳይያስ ራእዩን የተመለከተው “በዖዝያ፣ በኢዮዓታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን” ነበር፤ እዚህ ላይ “ዘመን” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ቀን ማለት ነው። (ኢሳ. 1:1) የኖኅና የሎጥ ዘመን (ቀን) ትንቢታዊ ትርጉም እንዳለው ተገልጿል። (ሉቃስ 17:26-30) “ቀን” የሚለው ቃል ተለዋዋጭ እንዲሁም ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው የሚያሳየው ሌላው ምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ “በይሖዋ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት” ነው በማለት የተናገረው ነው። (2 ጴጥ. 3:8) የዘፍጥረት ዘገባ ደግሞ አንድ የፍጥረት ቀን በሺህዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝመት እንዳለው ያመለክታል። (ዘፍ. 2:2, 3፤ ዘፀ. 20:11) “ቀን” ለሚለው ቃል የተሰጠውን ትርጉም ልንረዳ የምንችለው የቃሉን አገባብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማገናዘብ ነው።
9 ሰዓት፦ አንድን ቀን በ24 ሰዓት መከፋፈል የጀመሩት ግብፃውያን እንደሆኑ ታውቋል። አንድን ሰዓት በ60 ደቂቃዎች መከፋፈል የመጣው ግን በ60ዎች የተከፋፈለ የሒሳብ ስሌት ሥርዓት ከነበራቸው ባቢሎናውያን ነው። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ቀንን በሰዓት ስለ መከፋፈል የሚጠቅስ ነገር አናገኝም። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀኑን በተወሰኑ ሰዓቶች ከመከፋፈል ይልቅ “ጠዋት፣” “እኩለ ቀን” እና ‘ምሽት’ በሚሉት ቃላት ቀኑን ይከፋፍሉታል። (ዘፍ. 24:11፤ 43:16 የ1954 ትርጉም፤ ዘዳ. 28:29፤ 1 ነገ. 18:26) ሌሊቱ “ክፍለ ሌሊቶች” ተብለው በሚጠሩ ሦስት ጊዜያት የተከፈለ ሲሆን (መዝ. 63:6 የግርጌ ማስታወሻ) ሁለቱ ክፍሎች “መካከለኛው ክፍለ ሌሊት” እና (መሳ. 7:19) ‘የማለዳው ክፍለ ሌሊት’ በመባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተለይተው ተጠቅሰዋል።—ዘፀ. 14:24፤ 1 ሳሙ. 11:11
10 ይሁን እንጂ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ሰዓት” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ዮሐ. 12:23፤ ማቴ. 20:2-6) ሰዓት መቆጠር የሚጀምረው ከፀሐይ መውጫ ወይም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ሦስት ሰዓት” የሚል ሲሆን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ያለውን ጊዜ ማመልከቱ ነው። “ስድስት ሰዓት” ደግሞ ኢየሱስ ተሰቅሎ ኢየሩሳሌም ፍጹም ጨለማ የሆነችበት ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። ይህም የቀትሩን 6 ሰዓት ያመለክታል። ኢየሱስ በተሰቀለበት እንጨት ላይ የሞተበት ጊዜ “ዘጠኝ ሰዓት” እንደነበረ ተገልጿል።—ማር. 15:25፤ ሉቃስ 23:44፤ ማቴ. 27:45, 46
11 ሳምንት፦ የሰው ልጅ ቀኖችን በሰባት በሰባት ከፍሎ መቁጠር የጀመረው ከብዙ ጊዜ በፊት ነው። ይህን ያደረገው ስድስቱን የፍጥረት ቀናት ቀን ተብሎ በተጠራ ሌላ ሰባተኛ ቀን የቋጨውን ፈጣሪ ምሳሌ በመከተል ነው። ኖኅ ቀናትን ይቆጥር የነበረው በሰባት በሰባት ከፍሎ ነበር። በዕብራይስጥ “ሳምንት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ቃል በቃል ሰባት የሆነን ነገር ነበር።—ዘፍ. 2:2, 3፤ 8:10, 12፤ 29:27
12 የጨረቃ ወራት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ወር” ይናገራል። (ዘፀ. 2:2፤ ዘዳ. 21:13፤ 33:14፤ ዕዝራ 6:15) በዘመናችን ጊዜውን የምንቆጥረው የጨረቃን ዑደት መሠረት በማድረግ ስላልሆነ የጨረቃ ወር የለም። አንዱ የፀሐይ ዓመት ለ12 ተከፋፍሏል። የጨረቃ ወር ግን በአዲስ ጨረቃ መታየት የሚወሰን ወር ነው። አንድ የጨረቃ ወር በአማካይ የ29 ቀን፣ የ12 ሰዓትና የ44 ደቂቃ ርዝመት ሲኖረው በዚሁ ጊዜ ውስጥ አራት የተለያዩ የጨረቃ ደረጃዎች ይኖራሉ። የጨረቃው ወር የትኛው ቀን ላይ እንደሚገኝ የጨረቃዋን ቅርጽ በመመልከት ብቻ መገመት ይቻላል።
13 ኖኅ ሙሉ በሙሉ በጨረቃ ወራት ከመጠቀም ይልቅ የ30 ቀን ርዝመት ባላቸው ወራት ተጠቅሞ ታሪኩን የመዘገበ ይመስላል። በመርከቡ ውስጥ ይመዘግብ በነበረው መሠረት የጥፋቱ ውኃ ለአምስት ወራት ያህል ወይም “ለ150 ቀናት” በምድር ላይ እንዳየለ እንገነዘባለን። ወደ መርከቡ ገብተው የነበሩት ሰዎች ምድሪቱ ደርቃ ከመርከብ ሊወጡ የቻሉት ከ12 ወርና 10 ቀን በኋላ ነበር። ስለዚህ እነዚህ ታሪካዊ ክንውኖች የተፈጸሙባቸው ጊዜያት በትክክል ተመዝግበዋል ማለት ነው።—ዘፍ. 7:11, 24፤ 8:3, 4, 14-19
14 ወቅቶች፦ ይሖዋ ምድርን ለመኖሪያነት በሚያዘጋጅበት ጊዜ በፍቅሩና በጥበቡ ወቅቶች እንዲፈራረቁ አድርጓል። (ዘፍ. 1:14) ወቅቶች የሚፈራረቁት ምድር ፀሐይን በምትዞርበት ጊዜ 23.5 ዲግሪ ያህል በዛቢያዋ ላይ ዘንበል ስለምትል ነው። በዚህ ምክንያት በመጀመሪያ ደቡባዊው ንፍቀ ክበብ፣ ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ወደ ፀሐይ ዘንበል ይላል። ይህም ወቅቶች በቅደም ተከተል እንዲፈራረቁ ያደርጋል። ይህ የወቅቶች መለዋወጥ የመዝሪያና የመከር መሰብሰቢያ ጊዜያትን ከመቆጣጠሩም በላይ በዓመቱ ውስጥ የየራሳቸው ውበትና ባሕርይ ያላቸው ወራት እንዲኖሩ አስችሏል። ይህ የወቅቶች መፈራረቅ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር የአምላክ ቃል ዋስትና ሰጥቶናል። “ከአሁን ጀምሮ በምድር ላይ ዘር መዝራትና ማጨድ፣ ቅዝቃዜና ሙቀት፣ በጋና ክረምት እንዲሁም ቀንና ሌሊት ፈጽሞ አይቋረጡም።”—ዘፍ. 8:22
15 በተስፋይቱ ምድር አንዱን ዓመት ብራ የሚሆንበት የበጋ ወቅትና ዝናብ የሚዘንብበት የክረምት ወቅት በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል። ከሚያዝያ አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ እምብዛም ዝናብ አይኖርም። የዝናቡ ወቅት ደግሞ የፊተኛው ዝናብ ወይም ‘በልግ’ (ከጥቅምት እስከ ኅዳር)፣ ከባድ ዝናብ የሚዘንብበትና የቅዝቃዜ ወራት (ከታኀሣሥ እስከ የካቲት) እንዲሁም የኋለኛው ወይም “የጸደይ” ዝናብ (ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ) ተብሎ ሊከፈል ይችላል። (ዘዳ. 11:14፤ ኢዩ. 2:23) በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው የአየር ሁኔታ ስለሚለያይ ይህ አከፋፈል አንድ ወጥና የተስተካከለ ነው ማለት አይቻልም። የፊተኛው ዝናብ ደርቆ የቆየውን መሬት ስለሚያለሰልስ ከጥቅምት እስከ ኅዳር ያለው ጊዜ ‘የሚታረስበትና ዘር የሚዘራበት’ ጊዜ ነው። (ዘፀ. 34:21፤ ዘሌ. 26:5) ከባድ ዝናብ በሚዘንብባቸው ከታኅሣሥ እስከ የካቲት ባሉት ወራት በረዶ የሚጥል ሲሆን በጥርና በየካቲት ወራት ከፍታ ባላቸው አካባቢዎች አየሩ ከዜሮ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች ሊቀዘቅዝ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዳዊት ኃያላን ሰዎች አንዱ የነበረው በናያህ “በረዶ በሚጥልበት ዕለት” አንበሳ እንደገደለ ይናገራል።—2 ሳሙ. 23:20
16 መጋቢትና ሚያዝያ (በዕብራውያን ከኒሳንና ከኢያር ወራት ጋር ይቀራረባል) ‘የበልግ ዝናብ’ የሚዘንብባቸው ወራት ናቸው። (ዘካ. 10:1) በበልግ ወራት የተዘራው ዘር እንዲያቆጠቁጥና ጥሩ አዝመራ እንዲያስገኝ የሚያስፈልገው የኋለኛው ዝናብ ይህ ነው። (ሆሴዕ 6:3፤ ያዕ. 5:7) በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው መከር የሚሰበሰብበት ወቅት ሲሆን እስራኤላውያን ኒሳን 16 ቀን የአዝመራቸውን በኩራት እንዲያቀርቡ አምላክ አዟቸዋል። (ዘሌ. 23:10፤ ሩት 1:22) ውበትና ደስታ የሞላበት ወቅት ነው። “በምድሩ ላይ አበቦች አብበዋል፤ ተክሎች የሚገረዙበት ጊዜ ደርሷል፤ በምድራችንም ላይ የዋኖስ ዝማሬ ተሰምቷል። የበለስ ዛፏ መጀመሪያ ላይ ያፈራቻቸው ፍሬዎች በስለዋል፤ የወይን ተክሎቹም አብበው መዓዛቸውን ሰጥተዋል።”—መኃ. 2:12, 13
17 ብራ የሚሆንበት የበጋ ወቅት የሚጀምረው በሚያዝያ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን በዚህ ወቅት በሙሉ ማለት ይቻላል በተለይ በባሕር ዳርቻዎች ባለው ገላጣ ሜዳና በስተ ምዕራብ በሚገኘው ቁልቁለት ላይ ከሰማይ የሚንጠባጠበው ጠል የበጋውን አዝመራ አለምልሞ ያቆየዋል። (ዘዳ. 33:28) ግንቦት እህል የሚሰበሰብበት ጊዜ ሲሆን የሳምንታት በዓል (ጴንጤቆስጤ) የሚከበረው በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ነው። (ዘሌ. 23:15-21) ከዚያ በኋላ የአየሩ ሙቀት እየጨመረና መሬቱ እየደረቀ ሲሄድ የወይን ዘለላዎች ይበስሉና ይሰበሰባሉ። ቀጥሎም እንደ ወይራ፣ ተምርና በለስ ያሉት ሌሎቹ የበጋ ፍሬዎች ይሰበሰባሉ። (2 ሳሙ. 16:1) የበጋው ወቅት አልቆ የፊተኛው ዝናብ ሲጀምር የምድሪቱ ፍሬ በሙሉ ተሰብስቦ ያልቃል። የዳስ በዓል ወይም የማደሪያው ድንኳን በዓል የሚከበረውም (በጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ) በዚህ ጊዜ ነው።—ዘፀ. 23:16፤ ዘሌ. 23:39-43
18 ዓመት፦ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላለው ቦታ ያደረግነው ጥናት “ዓመት” ወደሚለው ቃል ያመጣናል። ይህ ቃል መጠቀስ የጀመረው የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው። (ዘፍ. 1:14) “ዓመት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ሻናህ ሲሆን “መድገም፣ እንደገና መሥራት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው። አንድን የተወሰነ የጊዜ ዑደት ያመለክታል። በየዓመቱ የወቅቶች መፈራረቅ ስለሚኖር ትርጉሙ ይህ መሆኑ ተገቢ ነው። አንድ ዓመት ብለን የምንጠራው ምድር ፀሐይን አንዴ ለመዞር የሚፈጅባትን የጊዜ ርዝመት ነው። ይህ ጊዜ በምድር ላይ ለምንኖረው ለእኛ ያለው ትክክለኛ ርዝመት 365 ቀን 5 ሰዓት 48 ደቂቃ 46 ሴኮንድ ወይም 365 1/4 ቀን ያህል ነው። ይህ ትክክለኛው የፀሐይ ዓመት ተብሎ ይጠራል።
19 የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት፦ በጥንቱ የዕብራይስጥ የቀን አቆጣጠር መሠረት አንድ ዓመት የሚቆጠረው ከበልግ እስከ በልግ ነው። ይህ ዓይነቱ አቆጣጠር ለግብርና ኑሮ በጣም ተስማሚ ነው። ዓመቱ የእርሻና የዘር ሥራ በሚጀምርበት በጥቅምት ወር መጀመሪያ ገደማ ይጀምርና መከር ተሰብስቦ በሚያልቅበት ጊዜ ላይ ያበቃል። ኖኅ ዓመቱን የቆጠረው ከበልግ ወራት ጀምሮ ነው። የጥፋት ውኃ የጀመረው “በሁለተኛው ወር” ላይ እንደሆነ የመዘገበ ሲሆን ይህ ጊዜ ደግሞ ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ኅዳር ወር አጋማሽ ድረስ ይዘልቃል። (ዘፍ. 7:11) ዛሬም ቢሆን የበልጉን ወቅት የአዲስ ዓመት መጀመሪያቸው የሚያደርጉ ብዙ የዓለም ሕዝቦች አሉ። እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ከግብፅ ሲወጡ ይሖዋ የአቢብ ወር (ኒሳን) ‘የወሮች መጀመሪያ እንዲሆንላቸው’ ደንግጎ ነበር። በዚህም ምክንያት በጸደይ ጀምሮ በጸደይ የሚያልቅ ቅዱስ ዓመት ሊኖራቸው ቻለ። (ዘፀ. 12:2) ይሁን እንጂ አይሁዳውያን በአሁኑ ጊዜ የሚከተሉት የቀን አቆጣጠር ከጥንቱ የተለየ በመሆኑ አዲስ ዓመታቸው የሚጀምረው በበልግ ወራት ነው። የመጀመሪያ ወራቸው ቲሽሪ ነው።
20 የፀሐይና የጨረቃ ዓመት፦ እስከ ክርስቶስ ዘመን ድረስ አብዛኞቹ ብሔራት ጊዜያቸውን ይቆጥሩ የነበረው በጨረቃ ዓመት ሲሆን ከፀሐይ ዓመት ጋር እንዲጋጠም ለማድረግ በተለያዩ የማስተካከያ ዘዴዎች ይጠቀሙ ነበር። አሥራ ሁለት ወራት ያሉት ተራው የጨረቃ ዓመት የ354 ቀናት ርዝመት ያለው ሲሆን ወራቱ ደግሞ እንደ አዲሱ ጨረቃ አወጣጥ የ29 ወይም የ30 ቀን ርዝመት ይኖሯቸዋል። ስለዚህ የጨረቃው ዓመት የ365 1/4 ቀናት ርዝመት ካለው ከፀሐይ ዓመት በ11 1/4 ቀን ያጥራል። ዕብራውያን ይከተሉ የነበረው የጨረቃን ዓመት አቆጣጠር ነው። ይህ የዓመት አቆጣጠራቸው ከፀሐይ ዓመትና ከወቅቶች መፈራረቅ ጋር እንዲተካከል ለማድረግ ምን ዓይነት ማስተካከያ ያደርጉ እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ ነገር አይኑር እንጂ አስፈላጊ በሚሆንባቸው ጊዜያት ተጨማሪ ወይም 13ኛ ወር መጨመር ነበረባቸው። በኋላ ግን በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የዚህ የማስተካከያ 13ኛ ወር አጨማመር የተወሰነና የታወቀ ሥርዓት እንዲከተል ተደርጎ ባሁኑ ጊዜ ሜቶኒክ ሳይክል ተብሎ የሚታወቀው ዑደት ተጀመረ። በዚህ ሥርዓት መሠረት በ19 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሰባት ጊዜ በአይሁዳውያን ቀን አቆጣጠር መሠረት ከ12ኛው ወር ከአዳር በኋላ ቬአዳር ወይም “ሁለተኛ አዳር” የሚባል ወር ይጨመራል። በዚህ መንገድ ከፀሐይ አቆጣጠር ጋር እንዲስተካከል የተደረገው የጨረቃ አቆጣጠር ባለ 12ና ባለ 13 ወር ዓመት፣ የፀሐይና የጨረቃ (ሉኒሶላር) ዓመት ተብሎ ይጠራል።
21 የጁልየስ እና የጎርጎርዮስ ዘመን አቆጣጠር፦ የአንድ ዓመት መጀመሪያ፣ ርዝመትና አከፋፈል የሚወሰንበትና እነዚህ ክፍልፋዮች የሚመሩበት የአመዳደብ ሥርዓት የዘመን አቆጣጠር ወይም ካሌንደር ይባላል። የጁልየስን አቆጣጠር በ46 ዓ.ዓ. የደነገገው ጁልየስ ቄሳር ሲሆን ይህንንም ያደረገው ሮማውያን የጨረቃን ዓመት አቆጣጠር የሚተካ የፀሐይ ዓመት አቆጣጠር እንዲኖራቸው አስቦ ነው። በጁልየስ አቆጣጠር እያንዳንዱ ዓመት 365 ቀናት ሲኖሩት በየአራት ዓመቱ ግን 366 ቀናት ያሉት ዓመት ይኖራል። ይሁን እንጂ የጁልየስ አቆጣጠር ከትክክለኛው የፀሐይ ዓመት በ11 ደቂቃ እንደሚበልጥ ከጊዜ በኋላ ታወቀ። በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ይህ የ11 ደቂቃ ብልጫ ተጠራቅሞ አሥር ሙሉ ቀን ደርሶ ነበር። በዚህም ምክንያት ሊቀ ጳጳሳት ጎርጎርዮስ በ1582 መጠነኛ ማስተካከያ አደረገና ዛሬ የጎርጎርዮስ አቆጣጠር ተብሎ የሚጠራውን የዘመን አቆጣጠር ደነገገ። በሊቀ ጳጳሱ ትእዛዝ ከ1582 ዓመት ላይ 10 ቀን እንዲቀነስ ተደረገና በጥቅምት 4 ማግስት ያለው ቀን ጥቅምት 15 እንዲሆን ተደረገ። በጎርጎርዮስ አቆጣጠር መሠረት በየአራት ዓመቱ የሚጨመረው አንድ ቀን ለ400 አለ ቀሪ ሊካፈሉ በማይችሉ መቶ ዓመታት ላይ አይጨመርም። ለምሳሌ ያህል 1900 ዓመት ለ400 ስለማይካፈል አራተኛ ዓመት ቢሆንም አንድ ቀን አልተጨመረበትም። 2000 ዓመት ግን ለ400 ስለሚካፈል ተጨምሮበታል። በአሁኑ ጊዜ የፈረንጆች ወይም የአውሮፓውያን አቆጣጠር ብለን የምንጠራው በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሚሠራበት የዘመን አቆጣጠር የጎርጎርዮስ የዘመን አቆጣጠር ነው።
22 ትንቢታዊ “ዓመት”፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ “ዓመት” የሚለው ቃል እያንዳንዱ ወር የ30 ቀናት ርዝመት ያሉትን የ12 ወራት ወይም የ360 ቀናት ርዝመት ያለውን ጊዜ ያመለክታል። አንድ ምሁር ስለ ሕዝቅኤል 4:5, 6 የሰጡትን አስተያየት ልብ እንበል፦ “ሕዝቅኤል ያውቅ የነበረው የ360 ቀናት ርዝመት ያለውን ዓመት ነው ብለን ለማሰብ እንገደዳለን። ይህ ደግሞ የፀሐይም ሆነ የጨረቃ ዓመት አይደለም። እያንዳንዱ ወር 30 ቀናት የሆኑበት ‘አማካይ’ ዓመት ነው።”
23 ትንቢታዊው ዓመት “ዘመን” ተብሎ የተጠራበትም ጊዜ አለ። ራእይ 11:2, 3 ላይና ራእይ 12:6, 14 ላይ እንደምናስተውለው አንድ “ዘመን” 360 ቀናት ተብሎ ተቆጥሯል። በትንቢት ውስጥ አንድ ዓመት በአንድ “ቀን” የተመሰለበት ጊዜም አለ።—ሕዝ. 4:5, 6
24 የዜሮ ዓመት አለመኖር፦ የግሪክን፣ የሮማንና የአይሁድን ሊቃውንት ጨምሮ የጥንት ሕዝቦች የዜሮ ጽንሰ ሐሳብ አልነበራቸውም። ለእነሱ ሁሉ ነገር የሚጀምረው አንድ ብሎ በመቁጠር ነበር። የሮማውያንን ቁጥር ተምረህ የምታውቅ ከሆነ (I፣ II፣ III፣ IV፣ V፣ X፣ ወዘተ) ዜሮን የሚያመለክት ቁጥር ተምረህ ነበር? አልተማርክም፣ ምክንያቱም ሮማውያን ዜሮ የሚባል ቁጥር አልነበራቸውም። ሮማውያን በዜሮ ይጠቀሙ ስላልነበረ የዘመናችን አቆጣጠር መቆጠር የጀመረው ዜሮ ዓመት ተብሎ ሳይሆን 1 ዓ.ም. ተብሎ ነው። በዚህ የተነሳ አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አሥረኛና መቶኛ የሚባሉት ቁጥሮች ሊኖሩ ችለዋል። እነዚህ ቁጥሮች ኦርዲናል ቁጥሮች ተብለው ይጠራሉ። በዘመናዊው ሒሳብ የሰው ልጅ ያለው ግንዛቤ፣ ሁሉ ነገር የሚጀምረው ከዜሮ እንደሆነ ነው። ዜሮን የፈለሰፉት ሂንዱዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።
25 ስለዚህ አንደኛ፣ ሁለተኛ ወዘተ የሚባሉት ቁጥሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ሙሉውን ቁጥር ለማግኘት ሁልጊዜ አንድ መቀነስ የሚኖርብን በዚህ ምክንያት ነው። ለምሳሌ ያህል ስለ 20ኛው መቶ ዘመን በምንናገርበት ጊዜ ሙሉ 20 መቶ ዓመታት አልፈዋል ማለታችን ነው? አይደለም። ከዚያ ይልቅ 19 ሙሉ መቶ ዓመታትና ሌሎች ጥቂት ተጨማሪ ዓመታትን ማመልከታችን ነው። ሙሉ ቁጥሮችን ለማመልከት ግን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ዘመናዊው ሒሳብ 1፣ 2፣ 3፣ 10 እና 100 የመሰሉትን ቁጥሮች ይጠቀማል። እነዚህም መደበኛ ወይም ካርዲናል ቁጥሮች አንዳንድ ጊዜ “ሙሉ ቁጥር” ተብለው ይጠራሉ።
26 የዘመናችን አቆጣጠር ወይም ዓመተ ምሕረት መቆጠር የጀመረው ዜሮ ተብሎ ሳይሆን 1 ተብሎ ስለሆነ፣ ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ያሉትን ዘመናት ለመቁጠርም ዜሮ ብለን ሳይሆን 1 ዓ.ዓ. ብለን ወደ ላይ መቁጠር ስላለብን የማንኛውንም ዓመት ሙሉ ቁጥር ለማግኘት አንድ መቀነስ ይኖርብናል ማለት ነው። ስለዚህ 1990 ዓ.ም. ሲባል የዘመናችን አቆጣጠር ከተጀመረ 1,989 ሙሉ ዓመታት አልፏል ማለት ነው። ሐምሌ 1, 1990 ሲባል ደግሞ የዘመናችን አቆጣጠር ከተጀመረ 1,989 ዓመት ከግማሽ አልፏል ማለት ነው። ለዓመተ ዓለምም ይኸው ሕግ ይሠራል። ስለዚህ ከጥቅምት 1, 607 ዓ.ዓ. እስከ ጥቅምት 1, 1914 ዓ.ም. ስንት ዓመታት እንዳለፉ ለማስላት በ1,913 ላይ (የሚመጣውን ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ጭምር) 606ን (ያለፈውን ዓመት የመጨረሻ ሦስት ወራት ጨምሮ) መደመር አለብን። ውጤቱ 2,519 (ሲደመር 12 ወራት) ወይም 2,520 ዓመት ይሆናል። ወይም 2,520 ዓመት ከጥቅምት 1,607 ዓ.ዓ. በኋላ የትኛው ዓመት ላይ እንደሚያርፍ ማስላት ከፈለግህ በመጀመሪያ 607 ኦርዲናል ቁጥር ስለሆነ የሚያመለክተው 606 ሙሉ ዓመትን መሆኑን ልብ በል። መቁጠር የምንጀምረው ከታኅሣሥ 31, 607 ዓ.ዓ. ሳይሆን ከጥቅምት 1,607 ዓ.ዓ. ጀምረን ስለሆነ 606 ላይ በ607 ዓ.ዓ. መጨረሻ ላይ ያሉትን ሦስት ወራት እንደምራለን። አሁን 606 1/4ን ከ2,520 ዓመት ላይ እንቀንስ። ቀሪው 1,913 ከ3/4 ይሆናል። ከጥቅምት 1, 607 ዓ.ዓ. ጀምሮ 2,520 ዓመት ሲቆጠር 1,913 3/4 ዓመት ዓ.ም. ይሆናል። 1,913 ሙሉ ዓመት ደግሞ 1914 መጀመሪያ ላይ ሲያደርሰን ተጨማሪው ሦስት አራተኛ ዓመት ደግሞ ጥቅምት 1, 1914 ላይ ያደርሰናል።
27 ጠቋሚ ዓመታት:- አስተማማኝ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት አቆጣጠር ተለይተው በሚታወቁ ጠቋሚ ዓመታት ላይ የተመሠረተ ነው። ጠቋሚ ዓመት የሚባለው ሰፊ ተቀባይነት ያገኘና አስተማማኝ ማስረጃ የተገኘለት ታሪካዊ ወቅት ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተለይቶ ከተመዘገበ ዓመት ጋር የሚጋጠም ዓመት ነው። ይህን ዓመት እንደ መነሻ በመጠቀም ተከታታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክንውኖች የተፈጸሙበትን ጊዜ በአኃዝ ለይቶ ማወቅ ይቻላል። ይህ ዓይነቱ ጠቋሚ ዓመት አንዴ ተለይቶ ከታወቀ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ዕድሜና የነገሥታት የንግሥና ዘመንን በመጠቀም ወደፊት ወይም ወደኋላ ያሉትን ታሪካዊ ዓመታት ማስላት ይቻላል። በዚህ መንገድ ተለይተው ከሚታወቁ ዓመታት በመነሳት አስተማማኝ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት አቆጣጠር አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክንውኖች የተፈጸሙበትን ጊዜ ማመልከት እንችላለን።
28 ለዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያገለግል ጠቋሚ ዓመት:- የባቢሎን ከተማ በቂሮስ መሪነት በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሠራዊት መገልበጡ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በዓለማዊ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ ግንባር ቀደም ክንውን ነው። ይህ ክንውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዳንኤል 5:30 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። የተለያዩ የታሪክ ማስረጃዎች (ዲዮዶረስን፣ አፍሪካነስን፣ ዩሲቢየስን፣ ቶሌሚንና የባቢሎንን ጽላቶች ጨምሮ) ባቢሎን በቂሮስ የተገለበጠችው በ539 ዓ.ዓ. እንደሆነ ይስማማሉ። የናቦኒደስ ዜና መዋዕል ከተማይቱ የወደቀችበትን ወርና ቀን ያመለክታል። (ዓመቱ ግን ጠፍቷል።) ዓለማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች ባቢሎን የወደቀችው በጁሊየስ የዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 11, 539 ዓ.ዓ. ወይም በጎርጎርዮስ የዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 5 ቀን እንደሆነ አስልተውታል።a
29 ቂሮስ ባቢሎንን ድል ካደረገ በኋላና ድል በተደረገችው በዚህች አገር ላይ ገዢ በሆነበት አንደኛ ዓመት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ የሚያዝዘውን ዝነኛ አዋጅ አወጣ። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሚያመለክተው አዋጁ የወጣው በ538 ዓ.ዓ. መገባደጃ ላይ ወይም በ537 ዓ.ዓ. የጸደይ ወራት መዳረሻ ላይ ነበር። ይህም አይሁዳውያኑ በትውልድ አገራቸው ከሠፈሩ በኋላ ‘በሰባተኛው ወር’ ማለትም በቲሽሪ ወይም ጥቅምት 1, 537 ዓ.ዓ. ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው የይሖዋን አምልኮ እንዲያቋቁሙ በቂ ጊዜ ይሰጣቸዋል።—ዕዝራ 1:1-4፤ 3:1-6b
30 ለክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያገለግል ጠቋሚ ዓመት፦ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቋሚ ዓመት ጢባርዮስ ቄሳር አውግስጦስ ቄሳርን የተካበት ዓመት ነው። አውግስጦስ የሞተው ነሐሴ 17 ቀን 14 ዓ.ም. (በጎርጎርዮስ ዘመን አቆጣጠር) ሲሆን ጢባርዮስ በሮማ ምክር ቤት ንጉሠ ነገሥት ሆኖ የተሾመው መስከረም 15, 14 ዓ.ም. ነበር። አጥማቂው ዮሐንስ አገልግሎቱን የጀመረው በ15ኛው የጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ በሉቃስ 3:1, 3 ላይ ተገልጿል። እነዚህ ዓመታት አውግስጦስ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ ከተቆጠሩ 15ኛው ዓመት ከነሐሴ ወር 28 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ ወር 29 ዓ.ም. ያለው ዓመት ይሆናል። ጢባርዮስ በሮማ ምክር ቤት ከተሾመበት ጊዜ ጀምረን ብንቆጥር ደግሞ ከመስከረም ወር 28 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 29 ዓ.ም. ያለው ዓመት ይሆናል። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከአጥማቂው ዮሐንስ ስድስት ወር ገደማ በዕድሜ የሚያንሰው ኢየሱስ “30 ዓመት ገደማ” በሆነው ጊዜ ሊጠመቅ መጣ። (ሉቃስ 3:2, 21-23፤ 1:34-38) ይህ ደግሞ “ኢየሩሳሌምን ለማደስና መልሶ ለመገንባት ትእዛዝ ከሚወጣበት ጊዜ አንስቶ” መሲሑ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ 69 “ሳምንታት” (እያንዳንዳቸው የሰባት ዓመት ርዝመት ያላቸውና በድምሩ 483 ዓመታት የሚሆኑ ትንቢታዊ ሳምንታት) እንደሚያልፍ ከሚናገረው የዳንኤል 9:25 ትንቢት ጋር ይስማማል። (ዳን 9:24) ‘ትእዛዙ’ የወጣው በ455 ዓ.ዓ. በንጉሥ አርጤክስስ (ሎንጊማነስ) ሲሆን በዚያው ዓመት ትንሽ ቆየት ብሎ በኢየሩሳሌም እንዲፈጸም ያደረገው ነህምያ ነበር። ከ483 ዓመታት በኋላ ማለትም በ29 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ኢየሱስ በዮሐንስ ሲጠመቅና በአምላክ መንፈስ ቅዱስ ሲቀባ መሲሕ ወይም ቅቡዕ ሆነ። ኢየሱስ በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ መጠመቁና አገልግሎቱን መጀመሩ በዓመታቱ ‘በሳምንቱ አጋማሽ’ ላይ (ወይም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ) እንደሚገደል ከሚናገረው ትንቢት ጋርም ይስማማል። (ዳን. 9:27) የሞተው በጸደይ ወራት ስለሆነ የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱ የጀመረው በ29 ዓ.ም. የበልግ ወራት መሆን ይኖርበታል።c በተጨማሪም ኢየሱስ ሥራውን ሲጀምር 30 ዓመት ገደማ ሆኖት እንደነበረ ሉቃስ 3:23 ይነግረናል። ከላይ ያየናቸው ሁለት ማስረጃዎች ኢየሱስ በ2 ዓ.ዓ. የበልግ ወራት መወለዱን ያረጋግጡልናል።d
31 ጊዜ ይሮጣል:- “የጠበቁት ጀበና ቶሎ አይፈላም” የሚል የቆየ አባባል አለ። ያለ ሥራ ቁጭ ብለን ስንውል፣ አንድ ነገር የሚሆንበትን ጊዜ ስንጠብቅ ወይም ትኩረታችንን ጊዜ ላይ ብቻ ካደረግን ጊዜው በጣም አዝጋሚ ይሆንብናል። ሥራ ከበዛልን፣ በምንሠራው ሥራ የምንደሰት ከሆነ ወይም ትኩረታችንን በምንሠራው ሥራ ላይ ካደረግን “ጊዜው ይከንፍብናል።” ከዚህም በላይ ጊዜ ከልጆች ይልቅ ለአረጋውያን በጣም ፈጥኖ የሚያልፍ ይመስላል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የአንድ ዓመት ልጅ በዕድሜው ላይ አንድ ዓመት ሲጨምር የሕይወት ተሞክሮው 100 በመቶ ጨመረ ማለት ነው። ሃምሳ ዓመት የሆነው ሰው በዕድሜው ላይ አንድ ዓመት ሲጨምር ግን የሚጨምረው የሕይወት ተሞክሮ 2 በመቶ ብቻ ነው። ለሕፃኑ አንድ ዓመት በጣም ረጅም ጊዜ ይሆንበታል። አረጋዊው ሰው ግን ጤነኛና ብዙ የሚሠራ ከሆነ ዓመታቱ ይበልጥ እየከነፉበት ይሄዳሉ። “ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም” የሚለው የሰለሞን ቃል ይበልጥ እየገባው ይሄዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች የሚገኙበት ዕድሜ አዳዲስ እውቀት የሚያገኙበት ወቅት በመሆኑ ጊዜ ቀስ ብሎ የሚያልፍ ይመስላቸዋል። በእነዚህ ዓመታት ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ‘ነፋስን ከማሳደድ’ ይልቅ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ብልጽግና ሊያጠራቅሙበት ይችላሉ። “አስጨናቂ የሆኑት ዘመናት ከመምጣታቸው እንዲሁም ‘ደስ አያሰኙኝም’ የምትላቸው ዓመታት ከመድረሳቸው በፊት በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ” የሚሉት የሰለሞን ቃላት በጣም ወቅታዊ ናቸው።—መክ. 1:9, 14፤ 12:1
32 ጊዜ፣ ሰዎች ለዘላለም ሲኖሩ፦ ይሁን እንጂ ጭንቀት የሚባል ነገር የማይኖርባቸው አስደሳች ቀናት ከፊታችን ይጠብቁናል። ‘የሕይወት ዘመናቸውን በይሖዋ እጅ’ የጣሉ ጽድቅ ወዳድ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። (መዝ. 31:14-16፤ ማቴ. 25:34, 46) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሞት አይኖርም። (ራእይ 21:4) ሥራ መፍታት፣ በሽታ፣ መሰልቸትና ከንቱነት ጨርሶ ቦታ አይኖራቸውም። የሰውን ልጅ ፍጹም ችሎታ የሚጠይቁና ጥልቅ እርካታ የሚያስገኙ አጓጊ ሥራዎች ይኖራሉ። ዓመታቱ እያደር እየፈጠኑና እየከነፉ የሚሄዱ ይመስላሉ። አድናቂና ትምህርት ተቀባይ የሆኑ አእምሮዎች አስደሳች ክንውኖችን በማስታወስ እየበለጸጉ ይሄዳሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ‘በአንተ ዘንድ ሺህ ዓመት፣ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን ነው’ ሲል ሙሴ እንደተናገረው ይሖዋ ለጊዜ ያለው አመለካከት ይበልጥ ይገባቸዋል።—መዝ. 90:4
33 አሁን ባለንበት ሰብዓዊ አቋም ላይ ሆነን የጊዜን ሂደት ስንመለከትና አምላክ የሰጠውን የአዲስ ዓለም ተስፋ ስናስተውል የዚያ ዘመን በረከቶች ምን ያህል አስደሳች ይሆኑልናል! “በዚያ ይሖዋ በረከቱን ይኸውም የዘላለም ሕይወትን አዟል።”—መዝ. 133:3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 1፣ ገጽ 453-4, 458፤ ጥራዝ 2፣ ገጽ 459
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 1፣ ገጽ 568
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2፣ ገጽ 899, 902
d ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2፣ ገጽ 56-8
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
የእስራኤላውያን ዓመት
የወሩ ስም ኒሳን (አቢብ)
የሚሸፍናቸው ወራት መጋቢት - ሚያዝያ
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 1ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 7ኛ ወር
በዓላት ኒሳን 14 ፋሲካ
ኒሳን 15-21 የቂጣ በዓል
ኒሳን 16 የፍሬ በኩራት መባ
የወሩ ስም ኢያር (ዚፍ)
የሚሸፍናቸው ወራት ሚያዝያ - ግንቦት
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 2ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 8ኛ ወር
ጥቅስ 1 ነገ. 6:1
የወሩ ስም ሲዋን
የሚሸፍናቸው ወራት ግንቦት - ሰኔ
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 3ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 9ኛ ወር
ጥቅስ አስቴር 8:9
በዓላት ሲዋን 6 የሳምንታት በዓል (ጴንጤቆስጤ)
የወሩ ስም ታሙዝ
የሚሸፍናቸው ወራት ሰኔ - ሐምሌ
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 4ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 10ኛ ወር
ጥቅስ ኤር. 52:6
የወሩ ስም አብ
የሚሸፍናቸው ወራት ሐምሌ - ነሐሴ
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 5ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 11ኛ ወር
ጥቅስ ዕዝራ 7:8
የወሩ ስም ኤሉል
የሚሸፍናቸው ወራት ነሐሴ - መስከረም
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 6ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 12ኛ ወር
ጥቅስ ነህ. 6:15
የወሩ ስም ቲሽሪ (ኤታኒም)
የሚሸፍናቸው ወራት መስከረም - ጥቅምት
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 7ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 1ኛ ወር
ጥቅስ 1 ነገ. 8:2
በዓላት ቲሽሪ 1 መለከት የሚነፋበት ቀን
ቲሽሪ 10 የስርየት ቀን
ቲሽሪ 15-21 የዳስ በዓል
ቲሽሪ 22 የተቀደሰ ጉባኤ
የወሩ ስም ሄሽቫን (ቡል)
የሚሸፍናቸው ወራት ጥቅምት - ኅዳር
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 8ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 2ኛ ወር
ጥቅስ 1 ነገ. 6:38
የወሩ ስም ኪስሌው
የሚሸፍናቸው ወራት ኅዳር - ታኅሣሥ
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 9ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 3ኛ ወር
ጥቅስ ነህ. 1:1
የወሩ ስም ቴቤት
የሚሸፍናቸው ወራት ታኅሣሥ - ጥር
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 10ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 4ኛ ወር
ጥቅስ አስቴር 2:16
የወሩ ስም ሺባት
የሚሸፍናቸው ወራት ጥር - የካቲት
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 11ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 5ኛ ወር
ጥቅስ ዘካ. 1:7
የወሩ ስም አዳር
የሚሸፍናቸው ወራት የካቲት - መጋቢት
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 12ኛ ወር
በአሁኖቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር 6ኛ ወር
ጥቅስ አስቴር 3:7
የወሩ ስም ቬአዳር
የሚሸፍናቸው ወራት (እንደ ጳጉሜ ያለ ጭማሪ ወር)
በጥንት አይሁዳውያን አቆጣጠር 13ኛ ወር