ሐና
[ሞገስ የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ]።
ሐና ነቢይት ስትሆን ከአሴር ነገድ የነበረው የፋኑኤል ልጅ ናት። ይህ የስሟ አጠራር ከግሪክኛ የተወሰደ ነው።
ሐና ለሰባት ዓመታት ብቻ በትዳር ከቆየች በኋላ ባሏ በመሞቱ መበለት ሆነች፤ ሕፃኑ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ በተወሰደበት ጊዜ የ84 ዓመት አረጋዊት ነበረች። ይሁን እንጂ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በቤተ መቅደሱ በማለዳ ከሚቀርበው አገልግሎት አንስቶ በምሽት እስከሚቀርበው አገልግሎት ድረስ አዘውትራ በዚያ ትገኝ ስለነበር ሕፃኑን ኢየሱስን ለማየትና ስለ እሱ ለመመሥከር በቅታለች። ‘መጾሟና ምልጃ ማቅረቧ’ በውስጧ ሐዘን እንዳለና በናፍቆት የምትጠብቀው ነገር መኖሩን ይጠቁማል። አይሁዳውያን በብዙ መቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሌሎች መንግሥታት መገዛታቸውም ሆነ ቤተ መቅደሱንም ሆነ የክህነት አገልግሎቱን ጭምር የነካው በብሔሩ የተስፋፋው የሃይማኖት ብክለት እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲሰማት እንዳደረገ መገመት አያዳግትም። ያም ሆነ ይህ፣ ሐና ሕፃኑ እስኪያድግ ድረስ በሕይወት እኖራለሁ ብላ ባትጠብቅም በዚህ መሲሕ በኩል ስለሚገኘው ነፃነት ለሌሎች በደስታ መሥክራለች።—ሉቃስ 2:36-38