መንግሥት
በአንድ ማኅበረሰብ፣ ቡድንና ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ተግባር የሚቆጣጠር መመሪያ ወይም ገደብ። በተጨማሪም የማስተዳደር ሥልጣን የያዘ ሰው፣ ቡድን ወይም ድርጅት።
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አርክሄ (መጀመሪያ) ከሚለው ቃል የተገኙት የተለያዩ ቃላት “መሳፍንት”፣ “መንግሥታት”፣ “መሪዎች”፣ “ሉዓላዊ ሥልጣናት” ተብለው በተለያዩ መንገዶች ተተርጉመዋል። (KJ; Dy; NW; AT; JB) በአንዳንድ ትርጉሞች “መንግሥት” ተብለው ለተተረጎሙት ኪበርኔሲስ እና ኪሪዮቴስ የሚሉ የግሪክኛ ቃላት ይበልጥ የሚቀርቡት ትርጉሞች ኪበርኔሲስ “መንዳት [መምራት ወይም አመራር መስጠት] እና ኪሪዮቴስ ደግሞ “ጌትነት” ናቸው። “ሥልጣን” (ኢሳ 22:21) የሚል ትርጉም ያለው ሜምሻላህ የሚለውና “ሥልጣን” ወይም “ገዢነት [ወይም መስፍናዊ አገዛዝ]” የሚል ትርጉም ያለው ሚስራህ የሚሉት ቃላት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “መንግሥት” ተብለው የተተረጎሙበት ጊዜ አለ።—ኢሳ 9:6
አምላክ ያቋቋማቸው በዓይን የማይታዩ ጥሩ መስተዳድሮች (ኤፌ 3:10) እንዲሁም ሰይጣንና አጋንንቱ ያቋቋሟቸው ክፉ መንግሥታት እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤፌ 6:12) የአምላክ ወኪል በመሆን በዓይን የማይታዩና የሚታዩ ጻድቅ መንግሥታትንና ሥልጣናትን መጀመሪያ ላይ ያቋቋመው ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። (ቆላ 1:15, 16) ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን የገዢነት ሁሉ ራስ አድርጎ ሾሞታል (ቆላ 2:8-10)፤ እንዲሁም በዓይን የማይታዩትም ሆኑ የሚታዩት ተቃዋሚ መስተዳድሮች ሁሉ እስኪደመሰሱ ድረስ መግዛት አለበት። (1ቆሮ 15:24) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ባለ መስተዳድር የሚመራ አዲስ ሥርዓት እንደሚመጣ ጠቁሞ ነበር።—ኤፌ 1:19-21
የዓለም መንግሥታት። መጽሐፍ ቅዱስ የዓለምን መንግሥታት “አራዊት” በማለት የሚገልጻቸው ሲሆን ሥልጣናቸውንም ያገኙት ከዘንዶው ይኸውም ከሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል። አምላክ እነዚህ መንግሥታት እንዲኖሩ የፈቀደላቸው ከመሆኑም ሌላ ከዓላማው ጋር በሚስማማ መልኩ ሥልጣናቸውንም ሆነ በሥልጣን የሚቆዩበትን ዘመን ገደብ አበጅቶለታል።—ዳን ምዕ 7, 8፤ ራእይ ምዕ 13, 17፤ ዳን 4:25, 35፤ ዮሐ 19:11፤ ሥራ 17:26፤ 2ቆሮ 4:3, 4፤ “BEASTS” እና “SYMBOLIC” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ክርስቲያኖችና መንግሥታት። ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በዘመናቸው በነበሩት ሰብዓዊ መንግሥታት ጉዳይ ጣልቃ ገብተው አያውቁም። (ዮሐ 6:15፤ 17:16፤ 18:36፤ ያዕ 1:27፤ 4:4) ክርስቲያኖች ለማኅበረሰቡ ደኅንነት አንድ ዓይነት መስተዳድር የግድ እንደሚያስፈልግ ስለተገነዘቡ ሕዝባዊ አብዮት ወይም ዓመፅ አነሳስተው አያውቁም። (ሮም 13:1-7፤ ቲቶ 3:1) ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” በማለት እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ሊከተሉት የሚገባ ጥሩ መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴ 22:21) ይህ መመሪያ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች (እንዲሁም ከዚያ ወዲህ የኖሩት ክርስቲያኖች) ከሰብዓዊ መንግሥታትና ከአምላክ መንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ትክክለኛውን ሚዛን እንዲጠብቁ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ ምድር ላይ እያለ፣ የእሱም ሆነ የደቀ መዛሙርቱ አቋም “ከቄሳር” ማለትም ከመንግሥታት ጋር መዋጋት ሳይሆን መንግሥታት የሚያወጧቸው ደንቦች ከአምላክ ሕግ ጋር የማይጋጩ እስከሆኑ ድረስ ከእነሱ ጋር ተስማምቶ መኖር እንደሆነ አሳይቷል። ጲላጦስም ቢሆን “ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም” ያለው ይህን ሐቅ ስለተገነዘበ ነበር። (ዮሐ 18:38) ሐዋርያትም የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለዋል።—ሥራ 4:19, 20፤ 5:29፤ 24:16፤ 25:10, 11, 18, 19, 25፤ 26:31, 32፤ “KINGDOM” እና “SUPERIOR AUTHORITIES” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።