ጊዜው እነርሱ ከሚያስቡት በላይ ወደፊት ገፍቶ ነበር
ጊዜው 609 ከዘአበ ሲሆን ቦታው ኢየሩሳሌም ነበር። ተናጋሪው ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስ ነው። እርሱ በሚወዳት ቅድስት ከተማው በኢየሩሳሌም ላይ ወደፊት ስለሚመጣው ጥፋት ትንቢት በመናገር ላይ ነው። ይህ ጥፋት የሚመጣው አይሁዶች በይሖዋ ላይ ጀርባቸውን በማዞራቸውና በሐሰት አማልክት አምልኮ ውስጥ በመዘፈቃቸው ምክንያት ነበር። እነርሱ በኮረብታዎች ላይ የረከሰ የጾታ አምልኮ ይፈጽሙ ነበር፣ ለዓረመኔ አማልክት የመጠጥ ቁርባን ያቀርቡ ነበር፣ ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትን ያመልኩ ነበር፣ እንዲሁም ለበዓል ያጥኑና ልጆቻቸውን ለሞሎክ መስዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር።—1 ነገ. 14:23, 24፤ ኤርምያስ 6:15፤ 7:31፤ 8:2፤ 32:29, 34, 35፤ ሕዝቅኤል 8:7-17
በእነርሱ ዓይን ኤርምያስ እንደ መርዶ ነጋሪ፣ መዓት ይመጣል እያለ የሚጮኽ ለፍላፊ፣ ሁሉንም ነገርና ሁሉንም ሰው የሚቃወም ግትርና አመጸኛ ሰው መስሎ ይታይ ነበር። ኤርምያስ ለ38 ዓመታት ያህል ሲያስጠነቅቃቸው ቆየ፤ ሆኖም ለ38 ዓመታት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ያፌዙበት ነበር። እስከዚሁ ጊዜ ድረስ ሕዝቡ ይሖዋን ከሐሳባቸው አውጥተውታል፤ ይሖዋ የሚያሳስባቸው ኃይል እንዳልሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። “[ይሖዋ (አዓት)] መልካም አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም” እንዲሁም “[ይሖዋ (አዓት)] ምድሪቱን ትቶአታል [ይሖዋም (አዓት)] አያይም” ይሉ ነበር።—ሶፎንያስ 1:12፤ ሕዝቅኤል 9:9
ነቢያቱ ኤርምያስና ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ሲሰብኩ ቢቆዩም ምንም የደረሰ ነገር አልነበረም። ስለዚህም እስራኤላውያን እንደዚህ ያለው ራእይ በእነርሱ ዘመን አይፈጸምም ብለው አሰቡ። “ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል” ይሉ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሰጠው ምላሽ የሚከተለው ነበር፦ “[ቀኖቹ ቀርበዋል (አዓት)] . . . እኔ [ይሖዋ (አዓት)] ነኝ፤ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፣ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፣ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ።”—ሕዝቅኤል 12:22-25
በ609 ከዘአበ ይሖዋ ቃሉን የሚፈጽምበት ጊዜ ደረሰ። ኤርምያስ ወደ አርባ ለሚጠጉ ዓመታት ማስጠንቀቂያውን ከተናገረ በኋላ የኢየሩሳሌም ከተማ በባቢሎናውያን ሠራዊት ተከበበች። ከአሥራ ስምንት ወራት በኋላም ግንቦችዋ ፈረሱ፣ ቤተመቅደሱ ተቃጠለ፣ አብዛኞቹም ሰዎች ወደ ባቢሎን ተማርከው ተወሰዱ። በትንቢት እንደተነገረውም ከተማዋ በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር ጠፋች።—2 ነገሥት 25:7-17፤ 2 ዜና 36:17-20፤ ኤርምያስ 32:36፤ 52:12-20
ኤርምያስ ትክክል ነበር። ሕዝቡ ግን ተሳስተው ነበር። ጊዜው እነርሱ ካሰቡት በላይ አልቆ ነበር። ራእዩ ገና ብዙ ዓመታት የሚቆይ አልነበረም። በዘመናቸው የሚፈጸም ነበር።
ይህ እንዲሁ ታሪክ ብቻ አይደለም። በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ነገር ትንቢታዊ ነበር። ገና ሊመጣ ላለ ጥላ ሆኖ ያገለግላል። የዛሬዋ ሕዝበ ክርስትና የክርስቶስን ስም በመውሰድ ከአምላክ ቃል ኪዳን እንደተጋባች ትናገራለች። ሆኖም የጥንት ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሄዱበትን መንገድ ትከተላለች። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ዓረመኔያዊ ትምህርቶች ታስተምራለች፣ በጾታ ብልግና የተበከለች ናት፣ ለፖለቲካ ዕቅዶች ድጋፏን ትሰጣለች፣ የዓለምን ጦርነቶች ትደግፋለች፣ ዝግመተ ለውጥን በመቀበል የአምላክን ፈጣሪነት ወደ ጎን ታደርጋለች፣ የሰዎችን ምቾት ለመጠበቅ ሲባል በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ያልተወለዱ ሕፃናት ሲሰዉ እንዳላየች ሆና ታልፋለች። በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስ አፈ ታሪክና ተረት ነው በማለት የሰው ፍልስፍናዎችን ትቀበላለች።
የኢየሩሳሌም ሕዝብ በኤርምያስ ላይ ያሾፉ እንደነበረው ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ዛሬ በይሖዋ ምስክሮች ላይ ታሾፋለች። በአርማጌዶን ስለሚመጣው ስለ መጪው ጥፋት ምስክሮቹ የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያ ዋጋ ቢስ እንደሆነ አድርጋ ትቆጥረዋለች። ሕዝበ ክርስትና ‘አምላክ ስለ ምድር ምንም ግድ የለውም’ ትላለች። ‘እርሱ ሰማዩን ያስተዳድር፤ እኛ ደግሞ ምድርን እናስተዳድራለን። አርማጌዶን ቢመጣም በእኛ ዘመን አይመጣም። ይህንን ታሪክ በፊትም ሰምተነዋል። ስለዚህ በመጨነቅ ጊዜያችንን አናጠፋም።’ የሚል ዝንባሌ አላት።
ታሪክ እንደገና ሊደገም ይሆን? ጊዜው በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ አልቆ እንደነበረ የሚገነዘቡበት ሰዓት ይመጣ ይሆን?