የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ይሖዋ እርዳታ ይሰጣል
በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራቸው የታገደበት ተጎራባች አገር ከሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው የሚያሳዝን መከራ ዜና ደረሳቸው። አሰቃቂ ድርቅ በመኖሩ የተነሣ ወንድሞቻቸው የሚኖሩት አንዳንድ ሥራሥሮችን እየበሉ መሆኑ ተነገራቸው። ተገቢ ልብስም አልነበራቸውም። ይህም አንዳንድ ምሥክሮችን በመስክ አገልግሎቱ ከመካፈል ወደኋላ እንዲሉ አድርጓቸዋል።
የደቡብ አፍሪካ ወንድሞች ወዲያውኑ ምላሽ ሰጡ። ልብስ ስለማስፈለጉ በጆሐንስበርግ አካባቢ ላሉ ጉባኤዎች ጥሪ ተደረገ። በቀናት ውስጥ ሦስት ቶን ልብስ ተዋጣ። ከዚያም ፈቃደኛ ወንድሞች ልብሶቹን በዓይነታቸው ለዩ። 3 ቶን ባቄላ፣ 1 ቶን ዘይት፣ 1 ቶን ሳሙናና 17 ቶን የበቆሎ ምግብ ለመላክ ዝግጅት ተደረገ። የበቆሎ ምግቡን ያቀረበው ኩባንያ በድርቅ በተመታው አገር የሚኖሩ ምሥክሮችን ችግር ሲሰማ የዚህን በጣም ተፈላጊ ምግብ ከአንድ ቶን በላይ አዋጡ።
ሚያዝያ 6, 1990 ሰኞ ዕለት የዕርዳታ ዝግጅቶቹን 25 ቶን ጭነት የያዘ የጭነት መኪና ከደቡብ አፍሪካ ተነስቶ የ3,400 ማይል ጉዞውን ተያያዘው። ይሁን እንጂ ወደዚህ በጦርነት ወደተቦጫጨቀ አገር ዕርዳታውን ለማስገባት ከባለሥልጣኖቹ ፈቃድ መገኘት ነበረበት።
የቆንሲል ባለሥልጣኖቹም የይሖዋ ምሥክሮች ባገራቸው (ሕጋዊ) እውቅና ባይኖራቸውም ስለመኖራቸው በደንብ እንደሚያውቁ ተናገሩ። የዕርዳታ አቅርቦቱን ወደ ወንድሞቻችን ለመላክ ምንም ተቃውሞ አልነበረም። ፈቃድ ተሰጠ። አስፈላጊዎቹ ሰነዶች ተሰጡና ዓርብ ሚያዝያ 20 ምሥክሮቹ ድንበሩን ያለአንዳች ችግር አቋረጡ። ይሁን እንጂ ሰነዳቸውን እንዲያሳዩ ብዙ ጊዜ የተጠየቁባቸው ከሰላሳ በላይ የመንገድ ኬላዎች (ፍተሻ ጣቢያዎች) አጋጠሟቸው። ያን ጊዜ ነበር እነዚያ ሰነዶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበሩ የተገነዘቡት።
ወደ አገሪቱ ገብተው 90 ማይሎች ያህል ከተጓዙ በኋላ ጉዞአቸው በአንድ በጎርፍ በተጥለቀለቀ ትልቅ ወንዝ ታገደ። የመጀመሪያው ድልድይ ስለተበላሸ በቦታው የተሠራው ጊዜያዊ ድልድይ ለትልቅ የጭነት መኪና መሄጃ ተስማሚ አልነበረም። ይሁን እንጂ በአጀቡ ውስጥ የነበሩት ትናንሽ ተሽከርካሪዎች በጐርፍ የተጥለቀለቀውን ድልድይ በደህና ሊያቋርጡት እንደሚችሉ ተገነዘቡ። አጀቡን ለሁለት ጓድ ለመክፈል ተወሰነ። አንዱ ጓድ ወደ ሰሜን 160 ማይሎች ርቀው ያሉትን ወንድሞች ለመገናኘት ሲሄዱ ቀሪው አንድ ጓድ በጐርፍ በተጥለቀለቀው ወንዝ አጠገብ ሠፈር (ድንኳን) ተከለ። በመጨረሻ ከወንድሞች ጋር ሲገናኙ እንዴት ተደሰቱ! ፈገግታቸውን፣ መተቃቀፋቸውንና እጅግ መጨባበጣቸውን ሊያቆሙ አልቻሉም። ወዲያውኑ በወንዙ ዳር የሚጠብቁትን ወንድሞች ለመገናኘት ሁለት የአካባቢው የጭነት መኪናዎች ጉዞ ጀመሩ። እዚያም የእርዳታ ዕቃዎቹ ከትልቁ የጭነት መኪና ወደ ትንንሾቹ ተዘዋወረ።
የደረሱት ሪፖርቶች የሚያመለክቱት ለይሖዋ የቁሳዊ እርዳታ ዝግጅት ጥልቅ ምሥጋናን ነበር። ሆኖም ከአካላዊ ጉስቁልናቸውም በላይ ለመንፈሳዊ ምግብ ወንድሞች ያሰሙት ጩኸት የበለጠ የሚያሳዝን ነበር። አንድ ጉባኤ የሚያገኘው አንዲት (ቅጂ) መጠበቂያ ግንብ ብቻ ስለነበር ያች እንደገና ለእያንዳንዱ ቤተሰብ እንድትዳረስ መገልበጥ ነበረባት። ለይሖዋ ምሥጋና ይገባውና አሁን በዚያ አገር ላሉ ወንድሞች የማያቋርጥ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ነው።