ሳይንስ ተዓምራት ሊፈጸሙ እንደማይችሉ ሊያረጋግጥ ይችላልን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት ተዓምራት በእርግጥ ተደርገዋልን? አልተደረጉም የሚሉ ብዙ ሳይንቲስቶችና ሃይማኖታዊ መሪዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ተአምራት የሚታመነው አጉል እምነት በነበረበት የጥንት ዘመን እንደሆነና ዘመናዊ ሳይንስ እነዚህ ተአምራት ሊፈጸሙ አለመቻላቸውን እንዳረጋገጠ ሆኖ ይሰማቸዋል። ስለዚህ ዘ ታይምስ በተባለው የለንደን ጋዜጣ ላይ የታተመ ብዛት ያላቸው ሳይንቲስቶች የፈረሙበትን የሚከተለውን ደብዳቤ ልብ ልንለው የሚገባ ነው። እንዲህ ይላል፦
“ተዓምራት ሊፈጸሙ አለመቻላቸውን ለማረጋገጥ ሳይንስን ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ምክንያታዊ አይደለም። ተዓምራት ሊፈጸሙ አይችሉም ብሎ ማመንም ሊፈጸሙ ይችላሉ ብሎ የማመንን ያህል እምነት የሚያስፈልገው ነገር ነው። . . . ተዓምራት ተደርገው የማያውቁ ድርጊቶች ናቸው። በዘመናችን ምንም ዓይነት የፍልስፍና አስተሳሰብ ቢኖር ወይም የሐሳብ መስጫ መመዘኛዎች የሚገልጹልን ሐሳብ ምንም ዓይነት ቢሆን (ቀደም ባሉት ጊዜያት የተፈጸሙትን ነገሮች በማጥናት ላይ የተመሠረተው) ሳይንስ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስረጃ ሊሆን እንደማይችል ማረጋገጡ በጣም አስፈላጊ ነው። የሳይንስ ‘ሕጎች’ በተሞክሮ ያስተዋልናቸውን ነገሮች በማጠቃለል የተደረሰባቸው ናቸው። እምነት ግን የተመሠረተው በሌሎች ነገሮች ላይ ነው።” (አይታሊክስ የጨመርነው እኛ ነን) በእርግጥም ዘመናዊ ሳይንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ተአምራት ሊፈጸሙ አይችሉም ብሎ ሊያረጋግጥ የሚችልበት መንገድ የለም።