የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
‘የመከር’ ሥራ በቬንዙዌላ
ኢየሱስ በአንድ ወቅት የስብከቱን ሥራ ከዓመታዊ የመከር ሥራ ጋር አመሳስሎ ነበር። (ማቴዎስ 9:36-38) የመከሩ ጌታ ይሖዋ አምላክ ሲሆን በምድር ዙሪያ ያለው መከርም በእርግጥም ታላቅ ነው። ይህ የመከር ሥራ እምብዛም ያልተሠራበትን የቬንዙዌላ ክልል ይጨምራል።
የቬኔዙዌላ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ አንድ የምሥክሮች ቡድን በጓሪኮ ክፍለ ሐገር በሚገኘው በሳባና ግራንድ ክልል ሲሠራ ያጋጠመውን ሁኔታ ዘግቧል። ምሥክሮቹ እንደሚከተለው በማለት ይተርካሉ፦ “የምናርፍበት ቤት ለስብሰባ የሚያመች ስለነበረ ወዲያውኑ እዚህ ቤት ውስጥ ስብሰባ ለማድረግ ሰዎችን መጋበዝ ጀመርን። ሰዎቹ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አያውቁም ነበር። በከተማው ውስጥ አራት የወንጌላውያን ቡድኖች ቢኖሩም ሕዝቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመማር ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው።
“ከቤት ወደ ቤት በማንኳኳትና ሰዎችን በሚቀጥለው ምሽት በምናደርገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ ጧት ለሦስት ሰዓት ከሰዓት በኋላ ደግሞ ለሦስት ሰዓት ሠራን። መቀመጫ ወንበሮች ስላልነበሩን የየራሳቸውን መቀመጫ ይዘው እንዲመጡ ጋበዝናቸው። ስብሰባው የሚጀምርበት ሰዓት ሲደርስ እያንዳንዳቸው መቀመጫቸውን ይዘው መምጣት ጀመሩ። ስብሰባው እንዳለቀ ነፃ የቤት መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ሁሉ ስማቸውን እንዲያስመዘግቡ ጠየቅን። በስብሰባው ላይ የተገኙት 29 ሰዎች በሙሉ ስማቸው እንዲመዘገብ ጠየቁ።
“እንግዶቻችን በሙሉ ወጥተው በሩን ልንዘጋ ስንል ሦስት ሰዎች በቤቱ ማዕዘን ተጠግተው መቆማቸውን ተመለከትን። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ራት ለመብላት ስንሰናዳ በሩን አንኳኩ። “በዚህ ከተማ የምታካሂዱት ይህ ስብከት ምንድን ነው? ዛሬ ማታ እዚህ ስብሰባ ያደረጋችሁት ለምንድን ነው?’ የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ጠየቁን።
“ሕግ ተላልፈን እንደሆነ ጠየቅናቸው። እነሱም ሕግ እንዳልተላለፍንና እነሱ በከተማይቱ ውስጥ ያሉት ሦስት የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያኖች ፓስተሮች ወይም ቄሶች እንደሆኑ ነገሩን። በዚያ ምሽት ቤተ ክርስቲያኖቻቸው ባዶ ስለቀሩ ተበሳጭተው ነበር። እንዲገቡ ጋበዝናቸውና ስለ ሥራችን ገለጥንላቸው። አንዳንድ ጽሑፎችንም አበረከትንላቸውና በሚቀጥለው ሐሙስ ተመልሰው እንዲመጡ ጋበዝናቸው።
“በተከታዩ ሐሙስ ፓስተሮቹ እኛ የምንለውን ለመስማት ከሚፈልጉ ሌሎች 22 ግለሰቦች ጋር ተመልሰው መጡ። ፓስተሮቹ እኛ ሴቶች ስለሆንን በውይይት የማንቋቋማቸው መስሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ በእኛ በኩል ስብሰባው የተሳካ ነበር። በመጨረሻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለመማር የሚፈልጉ ሰዎችን ስም እንደምንመዘግብ ገለጽንላቸው። ከፓስተሮቹ ጋር ከመጡት መካከል በርካታ ሰዎች ስማቸው እንዲመዘገብ ፈለጉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከእኛ ጋር አብረው በስብከቱ ሥራ ለመሠማራት ጠየቁን።
“እኛም በስብከቱ ሥራ ከእኛ ጋር ከመሄዳቸው በፊት ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀትና ልምምድ ወይም ማሠልጠኛ እንደሚያስፈልጋቸው ገለጽንላቸው። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንድናስረዳቸው ለመጠየቅ በየቀኑ ወዳለንበት ቤት ይመጡ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ማታ በጣም አምሽተን ስንነግራቸው ከቆየን በኋላ ወደቤታቸው እንዲሄዱ እንነግራቸው ነበር። መጨረሻ ከአካባቢው መሄድ ባስፈለገን ጊዜ በጣም አዘኑና ተመልሰን ስንመጣ ከእኛ ጋር መስበክ እንደሚጀምሩ ቃል ገቡልን። እስከምንመለስ ድረስ አስፈላጊውን መሻሻል እንደሚያደርጉ ቃል ገቡልን።”
ምሥክሮቹ ከዚያ ክልል ሲለቁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የፈለጉ ሰዎች ቁጥር 40 ደርሶ ነበር። የእነዚህ ሰዎች ስም 48 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ለሚገኝ በአቅራቢያው ያለ ጉባኤ ተላለፈለት። በኋላም ጥቂት ምሥክሮች ከሌላ ትልቅ ከተማ ወደዚህች ከተማ ተዛውረው መጡና ቀናተኛ የሆነ የምሥራቹ ሰባኪዎች ቡድን ሊቋቋም ቻለ።