“ከተለመደው በላይ የሆነ ታላቅ ኃይል”
አንድ ክርስቲያን ምን ያህል ሥቃይ ሊቋቋም ይችላል? በዛሬው ጊዜ በዓለም በሙሉ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ድህነት፣ የቤተሰብ መበታተን፣ ከፍተኛ ሐዘን የሚያስከትሉ ሁኔታዎች፣ በሽታ፣ ጦርነትና ስደት ያጋጥማቸዋል። ይህ ሁሉ ችግር እያጋጠማቸው ፍጹም አቋማቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ስለጻፈ ይቻላል። “ኃይል የሚሰጠኝ ስላለ ለማንኛውም ነገር የሚበቃ ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13 (አዓት)
ከይሖዋ የሚገኘው ኃይል ማንኛውንም ነገር ለመቋቋም የሚያስችል መሆኑን ታሪክ አረጋግጦልናል። ለምሳሌ ያህል በጀርመን አገር በናዚ የግዛት ዘመን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ብዙ መከራ ደርሶ ነበር። ታዲያ በደረሰባቸው መከራ ሁሉ ጸንተው ተገኝተዋልን? “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ናዚዝም” የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች [የይሖዋ ምሥክሮች] ብዙ ድብደባና ዛቻ፣ ብዙ ውርደትና እገዳ፣ እንዲሁም የማጎሪያ ካምፖች እሥራት ቢደርስባቸውም አንድም ጊዜ የናዚዎችን ትምህርት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም።”
ምሥክሮቹ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በነበሩባቸው ጊዜያት በእጅጌያቸው ላይ በሚደረግና የወይን ጠጅ ቀለም ባለው ባለሦስት ማዕዘን ጨርቅ ተለይተው ይታወቁ ነበር። ከሌሎቹ እሥረኞች የተለየ ከባድ ጭካኔ ይፈጸምባቸው ነበር። ይህ ሁሉ ሥቃይ አቋማቸውን ሊያስለውጣቸው ችሎአልን? ብሩኖ ቤተልሃይም የተባሉት የሥነ አዕምሮ ሊቅ እንዲህ ብለዋል፦ “ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሰብዓዊ ክብርና ሥነምግባር ከማሳየታቸውም በላይ እኔም ሆንኩ የሥነ አዕምሮ ተመራማሪዎች የሆኑት የሥራ ባልደረቦቼ በካምፑ ውስጥ የሚደርስባቸውን ነገር ሁሉ ለመቋቋም የሚያስችል የአዕምሮ ጽናት አላቸው ያልናቸውን ሰዎች እንኳን ሙሉ በሙሉ ያናጋውን ሁኔታ ለመቋቋም ችለዋል።”
አዎ፣ ማንኛውንም ነገር ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ነበራቸው። ይህን የመሰለ ኃይል የኖራቸው በይሖዋ ላይ ስለተመኩ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሎአል፦ “ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።” (2 ቆሮንቶስ 4:7) ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ይሖዋ እንደሚረዳህ እርግጠኛ ሆነህ የእሱን እርዳታ ጠይቅ። ይሖዋ ከሚሰጠው ታላቅ ኃይል ብርታት ስለምታገኝ ለመጽናት ትችላለህ።—ሉቃስ 11:13