የአምላክ ስም ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ
“የአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን የክርስቲያኖችም አምላክ የሆነው አምላክ ስም ‘JHWH’ ሠዓሊው አስቀምጦት ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት ወስዶአል። እሽቫርዝቨልደር ቦተ የተባለው የጀርመንኛ ጋዜጣ በደቡብ ጀርመን በሆርብ ከተማ በሚገኝ የከተማ አዳራሽ የፊት ለፊት ግድግዳ ላይ የአምላክ ስም ተመልሶ ስለመሳሉ ሲያትት የፃፈው ቃል ነበር። ይሁን እንጂ ስሙ ከቦታው እንዲፋቅ የተደረገው ለምን ነበር?
ጋዜጣው የከተማው አዳራሽ የውጭ ግድግዳው የፊት ለፊት ክፍል ለማስጌጥ ሲባል ሥዕላዊ ትርኢቶች ተቀብተውበት እንደነበር ይገልጻል። ከእነዚህም የቀለም ቅብ ሥዕሎች መካከል የአምላክን ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ይገኙ ነበር።
ጋዜጣው በመቀጠል “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ6,000 ለሚበልጥ ጊዜ የተጠቀሰው ይህ ስም ‘የሆቫ’ ወይም በጀርመንኛ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አጠራር ያለው ነው። በጽሑፍ የሰፈረው የዕብራይስጥ ቋንቋ ተነባቢ ሆሄያትን ብቻ የያዘ ስለነበር ትክክለኛው የስሙ አነባበብ በትክክል አይታወቅም። አናባቢያኑ የሚጨመሩት በአንባቢዎቹ ነበር” ይላል።
ይሁን እንጂ በ1934 የናዚ ፓርቲ ተጠሪዎች አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት “በወቅቱ ከነበረው ርዕዮተ ዓለም ጋር ስለማይስማማ” በላዩ ላይ ሌላ ቀለም ተደርቦ እንዲቀቡና እንዲጠፉ ወሰኑ። አራቱ ፊደላት አሁን ቦታቸው ላይ መመለሳቸው ያስደስታል። ጋዜጣው “ዛሬ (የከተማዋ አዳራሽ) የፊት ለፊት ግድግዳ በታሪካዊ ትርዒቶች፣ በጋሻ አርማዎችና በሥዕሎች ያጌጠ ስለሆነ በሆርብ ዐይን የሚስብ ቦታ ሆኖአል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቶአል።