አስገራሚ አምዶች ብቻ አይደሉም
አገር ጎብኚዎች በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘውና የጥንትዋ እስራኤል የባሕር ወደብ በሆነችው በቂሣርያ ያሉትን አምዶች ሲመለከቱ ስለ አምዶቹ ምንነት ተገርመዋል። ይህችን ወደብ የሠራው ታላቁ ሄሮድስ ሲሆን በአውግስጦስ ቄሣር ስም ሰይሞታል።
የመሬት ቁፋሮ አጥኚዎች አብዛኛውን የከተማ ክፍል፣ ትልቁን የጨዋታ መመልከቻ አዳራሽ ጭምር ቆፍረው አውጥተዋል። በተጨማሪም ወደቡ አሸዋማ በሆነው የባሕር ዳርቻ ላይ እንዴት እንደተገነባ ለመመልከት ባሕሩ ውስጥ ጠልቀው አይተዋል።
ከዚህ በፊት ወደ ባሕሩ ወጣ ብሎ በሚገኝ የቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ውስጥ አምዶች እንደተገኙ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (ጥር 8, 1991) ዘግቦአል። እነዚህ አምዶች ልዩ የሆኑት ከዚህ በፊት የማይታወቁ የሮማ ገዥዎች ስም ተጽፎባቸው ስለተገኘ ነው። ከተገኙት ጽሑፎች አንዱ የመርከቦች “ኃላፊ” የሚል ሲሆን “የመጀመሪያው የወደብ ከተማ እንደነበረች የሚያመለክት ጽሑፍ ነው።”
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለቱን ሚስዮናዊ ጉዞዎች ሲፈጽም እዚህ ወደብ ላይ አርፎ እንደነበረ ያውቃሉ። በወንጌላዊው ፊሊጶስ ቤት አርፎ ነበር። እዚያም የነበሩት ደቀመዛሙርት በጳውሎስ ተሞክሮ በጣም ሳይጽናኑ አልቀሩም። (ሥራ 18:21, 22፤ 21:7, 8, 16) እነዚህን አስደናቂ ተሞክሮዎች በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ለማንበብ እንችላለን።
ስለዚህ እነዚህ በባሕሩ ዳርቻ የሚገኙ አምዶች ምንም ዋጋ የሌላቸው የታሪክ ቅሪቶች አይደሉም። ክርስቲያኖች ምሥራቹን በወደቦችና “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” በትጋት ያዳረሱትን የጥንት ወንድሞቻቸውን እንዲያስታውሱ ያደርጉአቸዋል።—ሥራ 1:8
[በገጽ 32 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian