ከንቦች ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ
“ንቦች ከረዥም ዘመን ጀምሮ ያውቁት የነበረውን አንድ ነገር በቅርብ ዓመታት መሐንዲሶችና ፈልሳፊዎች ተገንዝበዋል። በጣም ስስ የሆነ አንድ ነገር ልክ እንደ ንብ እንጀራ ባለ ስድስት ጎን ሆኖ ቢሠራ ሌላ ዓይነት ቅርጽ ቢኖረው ከሚኖረው እጅግ የበለጠ ጥንካሬ ይኖረዋል።”—ጥቅምት 6, 1991 የኒውዮርክ ታይምስ
ሰዎች ጥቃቅን ነፍሳትን በጥንቃቄ ቢያጠኑ ብዙ ጥቅም ሊያገኙ መቻላቸው እንግዳ ነገር አይደለም። የጥንት የእምነት ሰው የነበረው ኢዮብ አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፣ ያስተምሩህማል የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፣ ይነግሩህማል . . . የ[ይሖዋ (አዓት)] እጅ ይህን እንዳደረገ ከነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?” (ኢዮብ 12:7-9) አዎ፣ የፈጣሪ ጥበብ ስድስት ጎን ባለው የንብ እንጀራ ውስጥ እንዳሉት ትናንሽ ክፍሎች በመሰሉት የተለመዱ ነገሮች በግልጽ ይታያል።
የእነዚህ ትናንሽ ክፍሎች የሰም ግድግዳ ውፍረቱ 1/3ኛ ሚሊ ሜትር የሚያክል ቢሆንም እጅግ በጣም ጠንካራ ነው። እንዲያውም ከራሱ ክብደት 30 ጊዜ የሚበልጥ ሸክም ሊሸከም ይችላል።
ይህ ጥንካሬ ተግባራዊ የሆነ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ መሣሪያዎችን ከንቅናቄና ከግጭት ለመከላከል ሊያገለግል ይችላል። በጃንጥላ አማካኝነት ከአየር ወደ ምድር የሚጣሉ የጦር መሣሪያዎች እንዳይሰበሩ በመከላከል ያገለግላል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ስለዚህ ጉዳይ ሲዘግብ “እንደ ጂፕ የመሰሉት ከባድ ዕቃዎች ከምድር ጋር ሲጋጩ እንዳይጎዱ በንብ እንጀራ ቅርጽ የተሠራ ማረፊያ ከሥራቸው ታስሮባቸው ይጣላሉ።”
በዚህ ንድፍ የሚሠሩ የተለያዩ እቃዎች ሰው ሰራሽ ከሆኑ ጥሬ ዕቃዎች ሊሠሩ ይችላሉ። በጣም የተለመደው ጥሬ ዕቃ ወረቀት ነው። ከናይለን ቃጫ የተሰራ ወረቀትና ሙጫ በንብ እንጀራ ቅርጽ ተሠርቶ በአንዳንድ ትላልቅ አውሮፕላኖች ክንፍ ውስጥ ይገባል። ክብደቱ አነስተኛ ሲሆን ጥንካሬው ግን በጣም ከፍተኛ ነው። ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? በቋሚ ግድግዳዎቹ መካከል ያለው ባዶ ቦታ በአብዛኛው የተሞላው በአየር ነው። በተጨማሪም አየሩ ጥሩ ሙቀት የመከላከል ችሎታ አለው።
ትንሽዋ ንብ የምህንድስና ዲግሪ ስለሌላት ይህንን ሁሉ የምትሠራው “አውቃ” አይደለም። ቢሆንም ፈጣሪዋ በሰጣት የባሕርይ ጥበብ እየተመራች ዕለታዊ ተግባርዋን ታከናውናለች።