“የጉብዝና ሚስትህ”
“ምንዝር ቀላል የዕለት ተዕለት ድርጊት የሆነ ይመስላል” ብዙ አዋቂዎች እንደዚህ ብለው እንደሚናገሩ ሎስ አንጀለስ ታይምስ ገልጿል። እንደዚህ ያለው አባባል ያስገርምሃልን? ይሁን እንጂ የሥነ አዕምሮ ጠበብት የሆኑት ፍራንክ ፒትማን 50 በመቶ የሚሆኑት ባሎች እንዲሁም ከ30-40 ከመቶ የሚደርሱ ሚስቶች በትዳራቸው ላይ እንደሚወሰልቱ ገምተዋል። ይህ አባባል እውነት ከሆነ ካገቡት ሰዎች መሐል ግማሾቹ ምንዝር ይፈጽማሉ ማለት ነው!
ታዲያ ይህ ማለት የፆታ ብልግና ትክክል ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! በየመንገዱ የሚፈጸመው ዓመጽ መብዛቱ አንድን ሰው መዝረፍን ትክክል እንደማያደርግ በትዳር ላይ መወስለት መስፋፋቱም የፆታ ብልግናን ትክክል አያደርገውም። የፆታ ብልግና መፈጸም ጎጂ ነው። ለምሳሌ ዛሬ ያለው የሰው ዘር ንጹህ የሆነ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ቢመራ በቀላሉ ሊከላከላቸው በሚችል በፆታ ግንኙነት አማካኝነት በሚተላለፉ አደገኛ በሽታዎች እየተጠቃ ነው። ሰዎች ለፆታ ስሜታቸው ልቅ ባይሆኑ ኖሮ ገዳዩ የኤድስ በሽታ እንደዚህ ሥር ባልሰደደም ነበር።
በተጨማሪም በጣም የሰለጠኑትና “ችግሩን የተረዱት” እንኳን የትዳር ጓደኞቻቸው ታማኞች ሳይሆኑ ሲቀሩ ብዙ ሥቃይ ይሰማቸዋል። አንድ ቃል ኪዳንን በማፍረስ የተፈፀመ መጥፎ ድርጊትን ከሚያደርሰው ቁስል ለማዳን ግማሽ የሕይወት ዘመን ሊያስፈልግ ይችላል።
ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነጥብ በጋብቻ መሐላ መወላወል የጋብቻ መሥራች ለሆነው አምላክ ክብር አለማሳየት ነው። ምክንያቱም የጋብቻ መሥራች አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን” ይላል። በተጨማሪም “ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።—ዕብራውያን 13:4
ስለዚህ ጥበበኛ ሰዎች “ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ” የሚሉትን በመንፈስ የተጻፉ ቃላት ይከተላሉ። (ምሳሌ 5:18) ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ለመደሰት ይፈልጋሉ። እንዲህ በማድረግ አካላዊና ስሜታዊ ጤንነታቸውን ይጠብቃሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለታላቁ የጋብቻ መሥራች ለይሖዋ አምላክ ክብር ያመጣሉ።