እውነተኛ ወንጌላዊ ያስገኘው መከር
ዊልያም አር. ብራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የሄደው በ1923 ነበር። ከሚስቱና ከልጁ ጋር ሆኖ በጋምቢያ፣ በጋና፣ በላይቤሪያ፣ በናይጄሪያና በሴራሊዮን የወንጌላዊነት ሥራ ሠርቶአል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) እርሱ የሠራው ሥራ ያስገኘው ውጤት በጣም የሚያስደንቅ ነው።
ይህ የዌስት ኢንዲስ ተወላጅ የሆነ ሰው የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን አባል አልነበረም። በፖለቲካ ጉዳዮችም ፈጽሞ አልገባም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስንና የሐዋርያትን አርአያ በመከተል የቤዛውን አስፈላጊነት አጉልቶ በመግለጽና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነት አሳውቆአል። (ማቴዎስ 9:35፤ 20:28፤ ዮሐንስ 17:4-6) ዊልያም አር. ብራውን ዘወትር በመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀም ነበር። በመሠረተ ትምህርትና በእምነት ጉዳዮችም እንደ መጨረሻ ባለሥልጣን አድርጎ የሚጠቅሰው መጽሐፍ ቅዱስን ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በዚህም ረገድ ጥብቅ የሆነ አቋም ስለነበረው ባይብል ብራውን እየተባለ ይጠራ ነበር።
ባይብል ብራውን የዘራቸው ዘሮች በይሖዋ በረከት አቆጥቁጠው አድገዋል። በአሁኑ ጊዜ እርሱ ባገለገለባቸው አገሮች 200,000 የሚያክሉ አፍሪካውያን ሕይወታቸውን ለፈጣሪያቸው ለይሖዋ ወስነው የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ሰዎች በመስበክ ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ 1 ቆሮንቶስ 3:6-9) እነዚህ ንቁ ክርስቲያኖች በሐቀኝነታቸውና እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ በመሆናቸው በሠፊው የታወቁ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸውና በመግዛት ላይ የሚገኘው ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ ተገዥዎች ለመሆን በመቻላቸው ኩራት ይሰማቸዋል።
ይህ መከር የእውነተኛ ክርስትና ወንጌላዊ ሥራ ያስገኘው ውጤት ነው። ሰው በሚኖርባቸው አህጉራት በሙሉ ይህንኑ የሚመስል መከር በዓለም በሙሉ በመሰብሰብ ላይ ነው። ከ200 በሚበልጡ አገሮች ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ ቅን ልብ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ተሰብስበው የሚከተለውን ወንጌላዊ መልአክ ቃላት በማስተጋባት ላይ ናቸው። “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት።” (ራእይ 14:7) እንደ እውነቱ ከሆነ በዚህ ሽብርና ብጥብጥ በበዛበት ዘመን ተስፋ ሊኖረን የሚችለው ወደ አምላክ ዘወር በማለትና ለንጉሣዊ ግዛቱ በመገዛት ነው።