ትንቢቱ ተፈጸመ
ኢየሱስ ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን የሚያሳይ ምልክት እንዲሰጣቸው በደቀ መዛሙርቱ በተጠየቀ ጊዜ ኢየሱስ “የዓመፃ ብዛት” እንደሚኖር ተንብዮ ነበር። (ማቴዎስ 24:3, 12) ይህ ትንቢት በዘመናችን እየተፈጸመ ነውን?
በእርግጥ እየተፈጸመ ነው! ጥቅምት 1991 ላይ በተባበሩት መንግሥታት የታተመው የተባበሩት መንግሥታትና ወንጀልን መከላከል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ያትታል፦ “ከባድ ወንጀል ለአብዛኞቹ የዓለም ብሔራት የተለየ ችግር ሆኗል። በአገራቸው ውስጥ የሚፈጸመው ወንጀል ከነጠላ ብሔራት ቁጥጥር አልፎ ሄዷል። እንዲሁም ከብሔራዊ ድንበሮች አልፎ የሚሄድ ወንጀል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን ከደረሰበት ደረጃ እጅግ አልፎ ጨምሯል። . . . በተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖች የሚፈጸመው ወንጀል በሚዘገንን ደረጃ በመስፋፋት በተለይ በአካላዊ ዓመፅ፣ ማስፈራሪያና የሕዝብ ባለ ሥልጣኖች ላይ ውድቀት በማምጣት በኩል ከባድ ውጤቶችን አስከትለዋል። ሽብር ፈጠራ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን የጉዳቱ ተጠቂዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለጥቅም ሲሉ ሌሎችን በመጉዳት ሱስ የሚያስይዙ አደንዛዥ ዕፆችን መነገድ ዓለም አቀፍ አሳዛኝ ነገር ሆኗል። በግዴለሽነት የሚደረግ አካባቢን የማጥፋት ወንጀል በጣም የሚያስደነግጥ መልክና ስፋት እየያዘ በመምጣቱ በዓለም በራሱ ላይ እንደሚፈጸም ወንጀል ተደርጎ ተቆጥሯል።”
ጥቃቶች፦ በ1970 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 150ዎቹ ጥቃት ይደርስባቸው የነበረ ሲሆን በ1990 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ስርቆት፦ በ1970 ከ100,000 ውስጥ 1,000 በላይ ብቻ ይደርስ የነበረው በ1990 ከ100,000 ውስጥ ወደ 3,500 በመድረስ ጨምሯል።
ዓለም አቀፍ የነፍስ ግድያዎች፦ ከ1975 እስከ 1985 ባሉት ዓመታት መካከል በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ከ100,000 ሰዎች ውስጥ ከ1 ወደ 2.5 ጨምሯል። ባደጉ አገሮች ደግሞ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ከ3 የሚያንስ የነበረው ወደ 3.5 በመድረስ ጨምሯል።
ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር የተያያዘ ወንጀል፦ መጽሐፉ ሲጠቅስ እንዲህ አለ፦ “ዋናዎቹ ነጋዴዎች አንድ ላይ ቢሆኑ የትንንሽ ብሔራትን መንግሥታት ቃል በቃል ብዙ ሊበልጡአቸው ወይም በጠብመንጃም ቢሆን ሊያሸንፉአቸው ይችላሉ። እንዲሁም እስካሁን ድረስ በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች ማገጃዎችና የሕግ አስከባሪዎች ላይ ችግር ሊፈጥሩባቸው ችለዋል።”
አጠቃላይ የወንጀል ቁጥር፦ በ1985 ከ100,000 ውስጥ 4,000 የነበረው በ2000 ዓመት ላይ በእጥፍ ጨምሮ 8,000 እንደሚደርስ ይጠበቃል።”
ዓለም አቀፍ የወንጀል መጨመር ግን ‘በዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ’ ላይ እንደምንኖር ከሚያመለክቱት የኢየሱስ ትንቢቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ “ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበች እወቁ” ብሏል።—ሉቃስ 21:31