“የሜዳ አበቦች”
ሥራ አጥነት። የዋጋ መናር። ድህነት። የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል። እነዚህ ቃላት በዜና መጽሔቶች ላይ እየጨመረ በሚሄድ ድግግሞሽ ይወጣሉ። እነዚህም ቃላት የሚያንፀባርቁት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብና ለማልበስ፣ እንዲሁም መጠለያ ለማግኘት በሚጣጣሩበት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ችግር ነው።
አማኞችም ሆኑ የማያምኑ በችግሩ ይነካሉ። ይሁን እንጂ አማኞች እነዚህን ችግሮች እንዲጋፈጡ ብቻቸውን አልተተዉም። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ ሲናገር “ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” ብሏቸዋል። — ማቴዎስ 6:26
እንዲሁም ኢየሱስ “የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?” ብሏል። — ማቴዎስ 6:28–30
ይህ ማለት አንድ ክርስቲያን ለመተዳደሪያው መሥራት አያስፈልገውም ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም! አንድ ክርስቲያን ወጪውን ለመሸፈን የሚያስፈልገውን ያህል በትጋት ይሠራል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ብሎ ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 3:10) ሆኖም ክርስቲያኑ ስለ አምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ እርግጠኛ ስለሆነ ሰማያዊ አባቱ እንደሚጠብቀው እምነት አለው። በመሆኑም የኑሮ ጭንቀቶች ሚዛኑን አያሳጡትም። በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳን ሳይቀር መቅደም ያለባቸውን ነገሮች ይኸውም መንፈሳዊ ነገሮችን ያስቀድማል። “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ያምናል። — ማቴዎስ 6:33