ለእምነቷ ስትል ተጋደለች
“ከሦስት ዓመታት በፊት በስፔይን አገር በካዲዝ ከተማ ውስጥ የምትኖር ካሪዳድ ባዛን ሊስታን የተባለች አንዲት የይሖዋ ምስክር አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና አስፈለጋት። በሃሞት ከረጢቷ ውስጥ የሚገኝ ጠጠር ደሟን እየመረዘባትና ከፍተኛ ትኩሳት እያስከተለባት ነበር። በአካባቢዋ ወደሚገኝ ሆስፒታል ስትገባ ደም ላለመውሰድ ያላትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አቋም ገለጸች። ሐኪሞቹም ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ሊያደርጉላት ተስማሙ። ይሁን እንጂ ቀዶ ሕክምና ወደሚደረግበት ክፍል ከመወሰዷ በፊት ሐኪሞቹ አንድ ሰነድ ላይ እንድትፈርም ጠየቋት። ሰነዱ ሐኪሞቹ ደምን በተመለከተ ያደረገችውን ውሳኔ ሊያከብሩላት ፈቃደኞች መሆናቸውን ይገልጽና ቀዶ ሕክምናው እየተካሄደ ለሚፈጠረው ድንገተኛ ሁኔታ አስፈላጊ ነው ብለው ያመኑበትን ማንኛውንም ዓይነት ሕክምና እንዲያደርጉላት የእሷን ፈቃድ የሚጠይቅ ነበር።
በሆስፒታሉ ተገኝቶ የነበረው የጉባኤ ሽማግሌና የይሖዋ ምስክር የሆነው የካሪዳድ ልጅ ይህንን ሰነድ መፈረም ምን ሊያስከትል እንደሚችል ገለጹላት። ሰነዱ ላይ ብትፈርም ኖሮ በቀዶ ሕክምናው ወቅት ሊከሰት በሚችል በማንኛውም ድንገተኛ ሁኔታ ሥር ሐኪሞቹ ደም እንዲሰጧት ይፈቅድላቸው ነበር። የሕክምና ፐርሶኔሉ ቀዶ ሕክምና ወደሚደረግበት ክፍል ሊወስዳት ሲመጣ ወረቀቱ ላይ እንደማትፈርም ነገረችው። ወደ ነበረችበት ክፍል እያዋከቡ ከመለሷት በኋላ ሐሳቧን እንድትቀይር ከፍተኛ ግፊት ያደርጉባት ጀመር።
በነገሩ ላይ ጥቂት ከተወያዩ በኋላ የሕክምና ዳኛ በማስጠራት እሷን ለማሳመን ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም። ካሪዳድ ደም እንዲሰጧት ብትፈቅድላቸው በአምላክ ፊት ኃጢአት እንደሠራች ሆኖ እንደሚሰማት ገለጸችላቸው። በሙሴ ሕግ አንዲት ሴት በፆታ ልትነወር ስትል ለእርዳታ ከጮኸችና ላለመደፈር ከታገለች እንደ ኃጢአተኛ እንደማትቆጠር በግልጽ ነገረቻቸው። (ዘዳግም 22:23–27) “ሐኪሞቹ ፍላጎቴን በመናቅ የሕሊናዬን ውሳኔ ለማስጣስ እየሞከሩ ናቸው። በዚህ ምክንያት አስገድደው በፆታ ሊያስነውሩኝ እንደፈለጉ ያህል ስለሚሰማኝ ልቋቋማቸ ው ይገባኛል” በማለት ተናገረች።
ጥቂት ሰዓታት አለፉ፤ በመጨረሻም ሐኪሞቹ ያለ ደም ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ተስማሙ። ካሪዳድ ቀዶ ሕክምናው በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ወደ ይሖዋ እንድትጸልይ አስፈቀደች። ጸለየች፤ ቀዶ ሕክምናውም በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ።
ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀኖች በኋላ ካሪዳድ ሕመሟ ስለጠናባት ሐኪሞቹ ያለውዴታዋ በግድ ደም እንዲሰጣት ወሰኑ። አንድ ሐኪምና አንዲት ነርስ ደም ሊሰጧት ተዘጋጁ። ምንም እንኳን በሽታው ካሪዳድን ያዳከማት ቢሆንም ባላት አቅም ሁሉ ደሙን ላለመውሰድ ታገለቻቸው። የሚሰጣት ደም የሚተላለፍበትን የላስቲክ ቱቦ ሳይቀር በጥርሷ ነከሰችው። በመጨረሻም ሐኪሙ እያደረጉ ባሉት ነገር ስላፈረ ደም የመስጠት ሙከራውን አቆመ። “በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልችልም፣ መሸነፌን አምኛለሁ!” ሲል ተናገረ።
ካሪዳድ ያንን ሁሉ ጣጣ ከተወጣች በኋላ ሌላ ተጨማሪ እክል ሳያጋጥማት ተሻላት። ሐኪሞቹም ሆኑ ነርሶቹ በእምነቷና ባሳየችው ድፍረት በጥልቅ ሳይነኩ አላለፉም። ካሪዳድ ይህ ሁሉ ነገር የደረሰባት በ94 ዓመቷ ነው።