ሰደድ እሳት ለኩሰህ ታውቃለህን?
ኧረ በጭራሽ፣ ትል ይሆናል። እስቲ ቆይ! ምናልባት ለኩሰህ ይሆናል። የደቀ መዝሙሩን የያዕቆብን ቃል አዳምጥ:- “አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፣ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።” — ያዕቆብ 3:5
ምላስ ለንግግር በጣም አስፈላጊ የሆነ ብልት ቢሆንም አላግባብ ተሠርቶበታል። ሰዎች ምላሳቸውን ለመዋሸትና የሰውን ስም ለማጥፋት ተጠቅመውበታል። በእሱም እየነቀፉ ሌሎችን አንቋሽሸዋል፣ መልካሙን ስማቸውን አጥፍተውባቸዋል፣ እንዲሁም ሸንግለዋል። ዓመፅ የሚያነሣሱ ሰዎች አብዮት ለማቀጣጠል በምላሳቸው ይጠቀማሉ። አዶልፍ ሂትለር በምላሱ ተጠቅሞ አንድን ብሔር ለጦርነት በማንቀሳቀስ ‘ሰደድ እሳት’ አቀጣጥሏል።
በመልካም ዓላማ ተነሣስተው የሚናገሩ ሰዎችም ቢሆን አነስተኛ ‘ሰደድ እሳት’ ሊያስነሱ ይችላሉ። አንድን ነገር ተናግረህ ወዲያውኑ ደግሞ ምነው ባልተናገርሁ ብለህ ታውቃለህን? ከሆነ ያዕቆብ “ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም” ሲል ምን ማለቱ እንደነበረ ይገባሃል። — ያዕቆብ 3:8
ያም ሆነ ይህ ምላሳችንን ለመልካም ነገር እንድንጠቀምበት ጥረት ማድረግ እንችላለን። እንደ መዝሙራዊው እኛም “በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ” በማለት ልንወስን እንችላለን። (መዝሙር 39:1) ሌሎችን እየነቀፍን ከመተቸት ይልቅ እነሱን ለመገንባት ጥረት ልናደርግ እንችላለን። የሰዎችን ስም ከማጥፋት ይልቅ መልካም ነገር ልንናገርላቸው እንችላለን። ከማጭበርበርና ከማታለል ይልቅ እውነቱን ልንናገርና ልናስተምር እንችላለን። በመልካም ልብ የምንገፋፋ ከሆነ ምላሳችን የሚያስደንቁ ፈዋሽ ቃላትን ሊናገር ይችላል። ኢየሱስ የሰው ልጆችን ስለ መዳናቸው በማስተማር ምላሱን በሚያስገርም መንገድ ተጠቅሞበታል።
በእውነትም “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው።” (ምሳሌ 18:21) ምላስህ ገዳይ ነው ወይስ ሕይወት ሰጪ? ‘ሰደድ እሳት’ ይለኩሳል ወይስ ያጠፋል። መዝሙራዊው ለአምላክ “ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 119:172) የመዝሙራዊውን ዓይነት አመለካከት በውስጣችን የምንኮተኩት ከሆነ እኛም ምላሳችንን ለመልካም ነገር እንጠቀምበታለን።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
U.S. Forest Service photo