ደም የመውሰድ ጠቃሚነት ተጋኗልን?
በዘመናዊው ህክምና ደም መውሰድ የተለመደ ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ የሚወራለትን ያህል ጠቃሚ ነውን? ምን ይመስልዎታል?
በአሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሜድስን (የካቲት 1993) ላይ ዶክተር ክሬግ ኤስ ኪችንስ:- “ደም የመውሰድ ጠቃሚነት ተጋኗል?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። ብዙውን ጊዜ ሐኪሞች አንድ ህክምና ያለው ጥቅም ሊያመጣ ከሚችለው አስጊ ሁኔታ የበለጠ እንደሆነና እንዳልሆነ ያመዛዝናሉ በማለት ገልጸዋል። ለበሽተኛ ደም መስጠትን በተመለከተ ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ኪችንስ እንደ ሄፐታይተስ፣ የሰውነት በሽታን የመቋቋም ኃይል መዳከም፣ የትልልቆቹ የሰውነት ክፍሎች መታወክና የተቀባዩ ደም ከሰጭው ደም ጋር አለመስማማቱ የሚያስከትለውን ጠንቅ የመሰሉ ደም ከመውሰድ ጋር የተያያዙ ብዙ አስጊ ሁኔታዎችን የሚገልጹ የቅርብ ጊዜ ማስረጃዎችን መለስ ብለው ተመልክተዋል። አንድ ጥናት ደም መውሰድ የሚያስከትላቸውን “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቀውሶች” ዘግቧል። “ሲያጠቃልልም ደም በተወሰደ ቁጥር 20 በመቶ መጥፎ ውጤቶችን የማስከተል አጋጣሚ አለው፤ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ቀላል ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ” አልፎ ተርፎም ሕይወትን ይቀጫሉ።
ይሁን እንጂ ይገኛሉ ተብለው ከታሰቡት ጥቅሞች አንጻር ሲታይ እንዲህ ዓይነቶቹ አስጊ ሁኔታዎችን መቀበሉ ተገቢ ነውን?
ዶክተር ኪችንስ ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ በማክበራቸው ምክንያት ደም አንወስድም ባሉት የይሖዋ ምስክሮች ላይ በተከናወኑ 1,404 ቀዶ ህክምናዎች ላይ የተካሄዱ 16 የጥናት ዘገባዎችን መርምረዋል። — ሥራ 15:28, 29
ውጤቱ ምን ሆነ? “የይሖዋ ምስክሮች ህሙማን ለከባድ ቀዶ ጥገኛዎች ደም አንወስድም የሚለው ውሳኔያቸው በቀዶ ህክምና የሚኖረውን የሞት አደጋ ከ0.5 በመቶ ወደ 1.5 በመቶ የሚያሳድገው ይመስላል። ደም ባለመውሰድ ምን ያህል የህመምና የሞት አደጋ እንደተወገደ ጎልቶ አልታየም፤ ይሁን እንጂ ደም ባለመውሰድ የተወገዱት አስጊ ሁኔታዎች ደም ባለመውሰድ ከሚኖሩት አስጊ ሁኔታዎች ይበልጡ ይሆናል።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ለመግለጽ የፈለጉት ነጥብ ምንድ ነው? ደም ባለመውሰድ የሚካሄደው ማንኛውም ህክምና የሚኖረው አደጋ ደም በመውሰድ ከሚኖረው አደጋ ሊያንስ ይችል ይሆናል የሚል ነው።
በመሆኑም ኪችንስ እንዲህ በማለት ምክንያታዊ ጥያቄ ያቀርባሉ:- “ደም ያልወሰዱ የይሖዋ ምስክሮች እምብዛም ጽኑ የሆነ በሽታና ሞት ካላስከተለባቸው እንዲሁም ከፍተኛ ጉዳትና በህክምናው ምክንያት የሚመጡ ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ማስወገድ ከቻሉ ሕሙማን ደም እንዲወስዱ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች ካሁኑ ማነስ ይኖርባቸው ይሆን?”
በእንዲህ ዓይነቱ ማስረጃ መሠረት ደም አንወስድም ያሉት ሰዎችም ከፈጣሪያችን መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እየተመላለሱ ነው።