የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በአምላክ ስም ተጠቅመው ነበርን?
በአራቱ ተነባብያን ፊደላት יהוה የሚወከለው (ይሖዋ) የሚለው የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ሺህ ጊዜ ተጽፎ ይገኛል። በከርሰ ምድር ተመራማሪዎች በቁፋሮ የተገኘው ማስረጃ እንደሚያሳየው እስራኤላውያን ከ607 ከዘአበ ማለትም ከግዞቱ በፊት ስሙን ዘወትር ይጠቀሙበት እንደነበረና ከግዞቱ በኋላ የተጻፉት እንደ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ ዳንኤል እና ሚልክያስ በተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ስሙ በተደጋጋሚ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ቀስ በቀስ ግን መሲሑ የሚመጣበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ አይሁዳውያን አጉል እምነት ያዙና በስሙ ከመጠቀም ወደኋላ ማለት ጀመሩ።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአምላክ ስም የሆነውን ይሖዋን (ብዙ ጊዜ “ጂሆቫ” ወይም “ያህዌህ” በመባል በእንግሊዝኛ የሚሠራበትን ቃል) ተጠቅመውበታልን? ማስረጃዎቹ አዎን ተጠቅመውበታል ይላሉ። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ስምህ ይቀደስ” ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ እርሱ ራሱ ወደ ሰማያዊ አባቱ ሲጸልይ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:6) ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተጠቀሙባቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም የሆነው የሴፕቱጀንት ቅጂዎች የአምላክን ስም በአራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት አስቀምጠው ነበር።
ስለ ወንጌሎችና ስለ ሌሎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችስ (“አዲስ ኪዳን”) ምን ሊባል ይቻላል? የአምላክ ስም በሴፕቱጀንት ውስጥ ይገኝ ስለነበረ ቢያንስ ቢያንስ የእነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጀመሪያ ቅጂዎች ከሴፕቱጀንት በጠቀሱባቸው ቦታዎች ላይ የአምላክን ስም ተጠቅመውበት መሆን አለበት የሚል ምክንያት ቀርቧል። ከዚህም የተነሣ ስሙ በአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ ከ200 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። አንዳንዶች ይህ የማያስፈልግ ነው ብለው ተችተዋል። ይሁን እንጂ ለአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ድጋፍ የሚሆን ያልታሰበ ምንጭ አለ። እርሱም የባቢሎናውያን ታልሙድ ነው።
የዚህ የአይሁዶች ሃይማኖታዊ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ሻባት (ሰንበት) የሚል ርዕስ አለው። እርሱም በሰንበት ቀን እንዴት መመላለስ እንደሚገባ የሚገልጽ ዝርዝር ሕጎችን የያዘ ነው። በአንዱ ክፍል ላይ በሰንበት ቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ከእሳት ማዳን ተገቢ ስለመሆኑ ውይይት እንደተደረገ ይገልጽና ከዚህ የሚከተለው ሐሳብ በጽሑፉ ላይ ሰፍሯል:- “በጽሑፉ ላይ ባዶ ቦታዎችንና [ጊልዮህኒም ] የሚኒም መጻሕፍትን ከእሳት ላናድናቸው እንችላለን የሚል ተጽፏል። ረቢ ጆሴ፣ ከሰንበት ቀን በቀር አንድ ሰው መለኮታዊውን ስም ብቻ ከጽሑፎቹ ላይ ቀድዶ አውጥቶ ከደበቀ በኋላ ሌላውን ክፍል ማቃጠል አለበት ብለው ተናገሩ። ረቢ ታርፎን ደግሞ፣ የልጄን ሥጋ! እነዚህ ጽሑፎች እጄ ላይ ቢገቡ ከመለኮታዊው ስማቸው ጋር አንድ ላይ አቃጥላቸዋለሁ በማለት ተናግረዋል። — የፍልስፍና ዶክተር በሆኑ በኤች ፍረድማን የተ ተረጎመ
ሚኒም የተባሉት እነማን ነበሩ? የቃሉ ትርጉም “መናፍቃን” ማለት ስለሆነ ሰዱቃውያንን ወይም ሳምራውያንን ሊያመለክት ይችላል። ነገር ግን ዶክተር ፍረድማን እንደሚሉት በዚህ ጽሑፍ ላይ የአይሁድ ክርስቲያኖችን የሚያመለክት ይመስላል። እንግዲያው እንደ ዶክተር ፍረድማን አባባል “ባዶ ቦታዎች” ተብለው የተተረጎሙት ጊልዮህኒም የተባሉትስ ምን ነበሩ? ሁለት አማራጭ ትርጉሞችን መስጠት ይቻላል። በጥቅልሉ ላይ የሚገኙ ያልተጻፈባቸው ኅዳጎች ወይም ምንም ያልተጻፈባቸው ጥቅሎች ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም በምጸት አነጋገር እንደ ባዶ ጥቅሎች ምንም የማይረቡ ናቸው ብሎ የሚኒም ጽሑፎችን ለመናቅ የተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል። በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ላይ ይህ ሁለተኛው ትርጉም “ወንጌሎች” ተብሎ ተጠቅሷል። ከዚህ ጋር በመስማማት በባቢሎናውያኑ ታልሙድ ላይ ከላይ ከተጠቀሰው የጽሑፉ ክፍል በፊት የሚገኘው ዐረፍተ ነገር “የሚኒም መጻሕፍት እንደ ባዶ ቦታዎች [ጊልዮህኒም ] ተደርገው ይቆጠራሉ” ተብሎ ይነበባል።
በዚህም መሠረት ሁ ወዝ ኤ ጅው? (አይሁዳዊው ማን ነበር?) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ሎውረንስ ኤች ሺፍመን ከላይ የተጠቀሰውን የታልሙዱን ክፍል እንደሚከተለው ተርጉመውታል:- “(በሰንበት ቀን) ወንጌሎችንና የሚኒም (‘የመናፍቃንን’) መጻሕፍት ከእሳት አናድናቸውም። ከዚህ ይልቅ እነሱንና የእነሱን ቴትራግራማታ (የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ፊደላት) እዚያው አገኘንባቸው ቦታዎች ላይ እናቃጥላቸዋለን። ረቢ ዮሴ ሀ–ገሊሊ በሳምንቱ መካከል አንድ ሰው ቴትራግራማታውን ቆርጦ አውጥቶ ከደበቀ በኋላ የቀረውን ማቃጠል አለበት አሉ። ረቢ ታርፎን፣ ልጆቼ ይሙቱ! (እነዚህ መጻሕፍት) እጄ ላይ ቢወድቁ ከቴትራግራማታቸው ጋር አብሬ አቃጥላቸዋለሁ ብለዋል።” ዶክተር ሺፍማን ቀጥለውም እዚህ ላይ ሚኒም የተባሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ናቸው ብለው ተከራክ ረዋል።
ይህ የታልሙድ ክፍል በእርግጥ የሚናገረው መጀመሪያ አካባቢ ስለ ነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነውን? ከሆነ፣ ክርስቲያኖች በወንጌሎቻቸውና በጽሑፎቻቸው ውስጥ የአምላክን ስም ማለትም ቴትራግራማተኑን ለመጠቀማቸው ጠንካራ ማስረጃ ነው ማለት ነው። እንዲሁም እዚህ ላይ ታልሙዱ የሚናገረው ስለ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነው ለማለት ያስደፍራል። እንደዚህ ያለው አመለካከት የምሁራን ብቻ ሳይሆን በታልሙዱ ውስጥ በዙሪያው ካሉት ሐሳቦች ተጨማሪ ድጋፍ አለው። ከላይ ካለው ከሻባት ከተጠቀሰው ሐሳብ ቀጥሎ ያለው ክፍል ከተራራው ስብከት የተወሰኑ ክፍሎች የገቡበትን ገማልያልንና አንድ ክርስቲያን ዳኛን የሚመለከት ታሪክ ይዟል።
ክርስቲያን ነን ባዮች በአምላክ ስም መጠቀም ያቆሙትና የአምላክ ስም ከሴፕቱጀንት፣ ከወንጌሎችና ከሌሎች መጻሕፍት እንዲወጣ የተደረገው ከሀዲ ክርስቲያኖች ቀላል ከሆኑት የኢየሱስ ትምህርቶች ፈቀቅ ካሉ በኋላ ብቻ ነበር።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ ዘመን የአምላክ ስም በ “ሴፕቱጀንት ” ውስጥ ይገኝ ነበር
[ምንጭ]
Israel Antiquities Authority