በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ ቀናተኛ ክርስቲያኖች
በእንግሊዝ አገር ከሚኖሩት 56 ሚልዮን ሰዎች መካከል በአሁኑ ወቅት ከ10 በመቶ የሚያንሱ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ናቸው በማለት ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት ተናግሯል። እሁድ እሁድ ከአራት ሚልዮን የሚያንሱ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። ከእነዚህም ውስጥ 1.1 ሚልዮን የሚያክሉት የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አባላት ናቸው። ምንም እንኳ አምላክ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል የሚለው አስተሳሰብ የተስፋፋ ቢሆንም የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥቱ ሃይማኖት በመሆን የምትጫወተው ሚና እንደቀጠለ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው መጽሔት “ብሪታንያ ክርስቲያን ኅብረተሰብ መሆኗን ካቆመች አያሌ ዓመታት አልፈዋል፤ ሆኖም አምላክ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል የሚለውን አስተሳሰብ ለመቀበል አሻፈረኝ ብላለች። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቷ ነገር ሁሉ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ቢመለስ የሚል ናፍቆት ስላላት ነው” በማለት ይናገራል። የዘመናችን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለው ዝምድና ተቋርጦ ቤተ ክርስቲያኗ እንድትፈርስ መጠየቃቸው ሊያስደንቀን አይገባም።
“ዓለማዊነት ያጠቃው ክርስቲያን ነኝ ብሎ የሚናገረው ዓለም በጣም መጥፎ ዓለም ነው” በማለት ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት የ19ኛው መቶ ዘመን ርዕሰ አንቀጽ አዘጋጅ የሆኑት ዋልተር ባጎት አማርረዋል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ‘እሱ የዓለም ክፍል እንዳልሆነ ሁሉ እነርሱም የዓለም ክፍል እንደማይሆኑ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) የአምላክን መንግሥት እንዲሰብኩ ወደ ዓለም ልኳቸዋል። ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምስክሮች በዓለም ዙሪያ “ሕዝብ ባለበትና ከቤት ወደ ቤት” እየሄዱ በቅንዓት በሚያከናውኑት ስብከት የታወቁ ናቸው። — ሥራ 20:20 አዓት
ከአንግሊካኖች ጋር ሲወዳደሩ 126,173 የሚያክሉት በብሪታንያ ውስጥ የሚገኙት ምስክሮች በቁጥር አናሳ ናቸው። ሆኖም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት በየወሩ 20 ሰዓት ገደማ ያሳልፋሉ። በተጨማሪም በ1992 እያንዳንዱ ምስክር በቅርቡ ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ዓለም የምታቋቁመውን መንግሥት ማለትም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ሰዎች በማስታወቅ በአማካይ ሌላ 16 ሰዓት አሳልፏል። (ማቴዎስ 24:14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የይሖዋ ምስክሮች በሚቀጥለው ጊዜ ወደ ቤታችሁ ሲመጡ ከሌሎች የተለዩ የሚያደርጋቸውን መልእክታቸውን ለመስማትና ቅንዓታቸውን ያነሣሳው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ትሞክራላችሁን?