እንደ ዛፍ
“እንደ እኔ ያለ ሞኝ ሰው ግጥም ይደርሳል፤ አምላክ ብቻ ግን ዛፍ መፍጠር ይችላል።” የግጥም ደራሲ የነበረው ጆይስ ኪልመር የዛፍን ውበት አድንቆ በሚጽፍበት ጊዜ ከላይ እንደተገለጸው በማለት ስለ እነርሱ መፈጠር ሊመሰገን የሚገባው አምላክ ነው ብሏል።
ይሖዋ አምላክ በዓይነታቸው ልዩ ልዩ የሆኑ፣ የተዋቡና የሚጠቅሙ ብዛት ያላቸውን ዛፎች ፈጥሯል። አጫጭርና ግዙፍ የሆኑ ዛፎች በቃላት መግለጽ እስኪያስቸግሩ ድረስ ውበት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ዛፎች ለምግብነት፣ ለማገዶነትና ለመጠለያነት ያገለግላሉ። ንድፍ አውጪዎች በእንጨት ልንገለገል የምንችልባቸውን አዳዲስ ዘዴዎች ማመንጨታቸውን ቀጥለዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ዛፎች መንግሥታትን፣ ገዥዎችንና ግለሰቦችን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ሕዝቅኤል 31:1–18፤ ዳንኤል 4:10–26) ዛፎች ከይሖዋ ንግሥናና ሕዝቡን እንደገና መልሶ ከማቋቋሙ የተነሣ ከሚኖረው ደስተኛ፣ ሰላማዊና ፍሬያማ ሁኔታ ጋር ተያይዘው ተገልጸዋል። (1 ዜና መዋዕል 16:33፤ ኢሳይያስ 55:12፤ ሕዝቅኤል 34:27፤ 36:30) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ሕዝቦች ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናል ይላሉ። (ኢሳይያስ 65:22) አንዳንድ ዛፎች ለብዙ መቶ ዓመታት መኖራቸውን ስንረዳ ይህ አባባል ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው መዝሙራዊ በአምላክ ሕግ ደስ የሚለው አንድ ሰው “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል። የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” በማለት ተናግሯል። ብዙ የውኃ ምንጮች ባሉበት ቦታ ላይ የበቀለ አንድ ያማረ ዛፍ መዝሙራዊውን ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚለው’ አንድ ሰው የሚያገኘውን መንፈሳዊ ብልጽግና አስታወሰው። (መዝሙር 1:1–3) በአምላክ ሕግና በቅዱስ ቃሉ የምትደሰት ከሆነ ዘመኖችህ ልክ እንደ ዛፉ ይሆኑልሃል። እንዲያውም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ካገኘኸው ትክክለኛ እውቀት ጋር ተስማምተህ ከኖርክ የዘላለም ሕይወትን ተስፋ በውስጥህ ልታሳድር ትችላለህ። — ዮሐንስ 17:3