የአምላክ ስም
“ይሖዋ ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ።” እንዲህ የሚነበበው በላቲን ቋንቋ የተቀረጸ አንድ ጽሑፍ ነው። ቃሎቹ የተመሠረቱት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው መዝሙር 127:1 ላይ ሲሆን ጥልቅ የሆነ እውነት ይዘዋል:- የይሖዋ በረከት የሌለበት ማንኛውም ጥረት በመጨረሻው ከንቱ ሆኖ ይቀራል።
በ1780 የተቀረጸው ይህ ጽሑፍ የሚገኘው በስሪ ላንካ ኮሎምቦ ውስጥ ባለ አንድ ሕንፃ ላይ ሲሆን ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የሚገኝበት ስለሆነ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። (ፎቶግራፉን ተመልከቱ) ይህ ስም በቀደሙት ዘመናት በሠፊው ይሠራበት ነበር። ብዙ ጊዜም ለመንፈሳዊ አገልግሎት በማይውሉ ሕንፃዎች፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በፍራንኮች ላይም እንኳን ሳይቀር ይቀረጽ ነበር። ሚስዮናውያን መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውን ይዘው ወደ ሩቅ አገሮች በሚሄዱበት ጊዜ በአምላክ ስም ይጠቀሙ ነበር። በስሪ ላንካ የተገኘው ይህ ጽሑፍ እንዲቀረጽ ያስቻለውም ይኸው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
ዛሬ ግን ሁኔታው እንዴት በጣም የተለየ ሆኖአል! ክርስቲያኖች ነን ከሚሉት ውስጥ ስለ አምላክ ስም ደንታ ያላቸው በጣም ጥቂት ናቸው። እንዲያውም የይሖዋ ምስክሮች ስለ አምላክ ስም አጥብቀው መናገራቸውን የሚነቅፉ አንዳንድ ምሁራን አሉ። ለምን? እንደ አንዳንዶቹ ምሁራን አባባል የአምላክ ስም የዕብራይስጥ አጠራር በትክክል ስለማይታወቅ ነው። ይሁንና የኢየሱስን ስም የመጀመሪያ የዕብራይስጥ አጠራር የሚያውቁ ስንት ሰዎች ናቸው? ሆኖም ስሙ በየትም ቦታ የሚሠራበትና የተከበረ ነው።
ለኢየሱስ የአምላክ ስም በጣም አስፈላጊ ነበር። “ስምህ ይቀደስ” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:9) ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎም ለአምላክ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” ብሎታል። (ዮሐንስ 17:6) እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ፈለግ ተከታዮች ናቸው። ታዲያ እነርሱም ‘የአምላክን ስም መግለጥ’ የለባቸውምን? የይሖዋ ምስክሮች የአምላክን ስም ይገልጣሉ፤ ይሖዋም የእነርሱን “ቤት” አብዝቶ ይባርካል። ለእነርሱ “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” የሚለው መዝሙር በትክክል ተፈጽሟል። — መዝሙር 144:15 አዓት