ሊጠቅሙዎት ይችላሉን?
በእጅዎ ያለው ይህ መጽሔት የማበረታቻ ምንጭ ለመሆንና ቤተሰብን ለመምራትም ሆነ በግል ንጹሕ አቋምን ለመጠበቅ የሚያገለግሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ለማስታወስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የዛሬዎቹ አስጨናቂ ቀናት እንደሚመጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ የተነገረ መሆኑን በማሳየት ለዚህ መፍትሔው የአምላክ መንግሥት መስተዳድር መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። እርስዎስ ከመጠበቂያ ግንብ እና የእርሱ ተጓዳኝ ከሆነው ከንቁ! መጽሔት ሊጠቀሙ ይችላሉን?
ቪልማ የተባለች አንዲት ሴት ከፊሊፒንስ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ጽሑፎቻችሁን ለመግለጽ ቢፈለግ ‘ግሩም ድንቅ ናቸው’ ማለትን እመርጣለሁ። የንቁ! እና የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶቻችሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋቸውና ያነበብኳቸው ከማኒላ ወደ መኖሪያ ቤቴ ስመለስ በአውቶቡስ ላይ እያለሁ ነበር። ብዙውን ጊዜ በጉዞ ላይ ስሆን መጽሔቶችን እያነበብኩ የመሄድ ልማድ ነበረኝ። በዚያን ጊዜ ግን ምንም መጽሔት አልያዝኩም ነበር።
“በጉዞው ላይ እያለን ከጎኔ ተቀምጦ የነበረው በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው የእናንተን ጽሑፎች ይዞ ነበር። የንቁ! መጽሔቱን ካነበበ በኋላ እንደገና ሌላ መጽሔት አወጣ፤ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ነበር። በዚህ ጊዜ የንቁ! መጽሔቱን የመዋስ አጋጣሚ አገኘሁ። እውነቱን ለመናገር ሁሉም የትምህርቱ ርዕሶች ማራኪ፣ ወቅታዊና የሚያነቃቁ በመሆናቸው እነዚያን መጽሔቶች ማንበቤ በጣም አስደስቶኛል።”
ይህች ሴት ስትደመድም እንዲህ ብላለች፦ “መጽሔቶቻችሁ እንዲደርሱኝ እፈልጋለሁ። እባካችሁ እንዴት ሊደርሱኝ እንደሚችሉ አሳውቁኝ።” በፊሊፒንስ የሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ይህችን ሴት መጽሔት ከሚላክላቸው ሰዎች አንዷ እንድትሆን ለመተባበር ደስተኛ ነበር።