እንደ ወርቅ ፖም
የፖም ፍሬ ሲያዩትም ሆነ ሲበሉት እንዴት አስደሳች ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጣፋጭ ፍሬ አእምሮን በሚያመራምር የማነጻጸሪያ ምሳሌ እንዲህ ሲል ይጠቀምበታል፦ “የወርቅ እንኮይ [ፖም አዓት] በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜውም ቃልም እንዲሁ ነው።” (ምሳሌ 25:11) ይህ አባባል ትርጉሙ ምንድን ነው?
“የወርቅ እንኮይ [ፖም አዓት] በብር ፃሕል ላይ” ሲል፣ ከብር ተቀርጾ በተሠራ ሳሕን ላይ ያለን የፍራፍሬ ቅርጽ ያለውን ወርቅ ሊያመለክት ይችላል። በዚህ በምዕራፍ ውስጥ ቀደም ያሉት ቁጥሮች በንጉሥ ፊት ስለመቅረብ ስለሚናገሩ፣ ይህ ቁጥር የፖም ቅርጽ ያላቸውን የወርቅ ጌጣ ጌጦች ከብር በተሠሩ ሳሕኖች ላይ አድርጎ ለአንድ ንጉሥ ገጸ በረከቶችን ማቅረብን ሊያመለክት ይችላል። (ምሳሌ 25:6, 7) በእውነቱ ይህ እንዴት የሚያምር አስደናቂ ስጦታ ነው!
ትክክለኛ የሆኑ፣ ክብር ያላቸውና በጥሩ ሰዓት ላይ የተነገሩ ወይም የተጻፉ ቃላትም ተመሳሳይ ውበት አላቸው። እንዲህ ያሉት ቃላት በብዙ መንገዶች አስደሳች፣ አበረታችና ጠቃሚ ናቸው። በተለይ ደግሞ በመለኮት አነሳሽነት የተጻፉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ቃላት ‘በብር ፃሕል ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም’ የተዋቡ ናቸው።
በምሳሌ 25:11 ላይ የሚገኘው ጥበብ ያለበት የንጉሥ ሰሎሞን አባባል እንደሚያሳየው፣ ሰሎሞን ‘ያማረውን በቅንም የተጻፈውን ትክክለኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፍለጋ አድርጓል።’ (መክብብ 12:10፤ ምሳሌ 25:1) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስም “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክሮችን፣ ትንቢቶችን፣ ሥዕላዊ አገላለጾችንና ጥሩ ችሎታ አላቸው የተባሉ አንጥረኞች ከሠሯቸው ጌጣጌጦች የበለጠ ውበት ያላቸውን አንጸባራቂ እውነቶች ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ጥበብ ያገኘ ሰው እጅግ ውድ የሆነ ንብረት አግኝቷል፤ እንዲሁም ለዘላለም ለመኖር በተስፋ ሊጠብቅ ይችላል።—ምሳሌ 4:7–9፤ ዮሐንስ 17:3