“ከማሾፋችን በፊት ብዙ እናንብብ”
ይህን የተናገረው አሁን የምታነበውን መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት ያነበበ በኒውዚላንድ የሚገኝ አንድ ሰው ነው። ይህ ሰው በሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 ላይ ስለ ተገለጸው ስለ ሰማያዊው የአምላክ ሠረገላ የሚናገረውን ጽሑፍ በተመለከተ እንደዚህ በማለት ጻፈ፦
“እነዚህ አራት ፍጥረታት ወይም ኪሩቤሎች እያንዳንዳቸው አራት አራት ክንፍ እና አራት አራት ፊት ነበራቸው። የአንበሳው ፊት የይሖዋን ፍትሕ ያመለክታል፤ የጥጃው ፊት የአምላክን ኃይል ያመለክታል፤ የንስሩ ፊት የእርሱን ጥበብ ያመለክታል፤ እንዲሁም የሰው ፊት ያላቸው መሆኑ የይሖዋን ፍቅር ያመለክታል።
“ይህንን ደጋግሜ ካነበብኩ በኋላ በልቤ ውስጥ የደስታ ስሜት ተሰማኝ። ዓይኖቼ የደስታ እንባ አቀረሩ። ወዲያውኑ ወደ አእምሮዬ የመጣልኝ ‘አንተ ይሖዋ፣ እንዴት የምታምርና ደስ የምታሰኝ ነህ!’ የሚል ሐሳብ ነበር። ዓለማዊ ሰው እንደ መሆኔ መጠን ለብዙ ዓመታት ሳሾፍበትና ስቀልድበት ለነበረው ይሖዋ ለተባለው ለዚህ አምላክ እንደዚህ የመሰለ አዲስ ስሜት እንዴት እንደ ተሰማኝ ለራሴም ገርሞኛል። የይሖዋ ምስክሮችን ‘አመሰግናችኋለሁ’ እላቸዋለሁ። እንደ እኔ ላሉ ለብዙዎች ደግሞ ‘ከማሾፋችን በፊት ብዙ እናንብብ’ እላቸዋለሁ።”