ሊታወስ የሚገባው ምሽት
በአንድ በማይረሳ ዕለት ይሖዋ አምላክ ከ3,500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በግብጽ አገር ባሪያዎች ሆነው ይኖሩ የነበሩትን እስራኤላውያን ጠቦት አርደው ደሙን በቤታቸው በር መቃንና በጉበኑ ላይ እንዲረጩ አዝዟቸው ነበር። በዚያው ሌሊት የአምላክ መልአክ ደም የተረጨባቸውን ቤቶች እያለፈ በግብጻውያን ቤቶች ውስጥ ያሉትን የበኩር ልጆች ገደለ። ከዚያም እስራኤላውያን ነፃ ወጡ። ከዚያ ጊዜ አንሥቶ አይሁዳውያን በየዓመቱ በዚያ ቀን የማለፍን በዓል ያከብሩ ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የማለፍን በዓል ለመጨረሻ ጊዜ ካከበረ በኋላ ወዲያውኑ የእርሱን መሥዋዕታዊ ሞት የሚያስታውስ ራት እንዲከበር ደነገገ። ለታማኝ ሐዋርያቱ ቂጣ ሰጣቸውና “እንካችሁ ብሉ፣ ይህ ሥጋዬ [ማለት አዓት] ነው” አላቸው። ከዚያም የወይን ጠጅ ጽዋ ሰጣቸውና “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” አለ። ጨምሮም ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። (ማቴዎስ 26:26–28፤ ሉቃስ 22:19, 20) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ተከታዮቹ ሁሉ ይህን የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ አዘዛቸው።
የይሖዋ ምስክሮች በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርቡልዎታል። በቤትዎ አቅራቢያ ወደሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ በመሄድ በዓሉን ማክበር ይችላሉ። ትክክለኛውን ሰዓትና ቦታ ለማወቅ በአካባቢዎ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮችን ይጠይቁ። በ1994 በዓሉ የሚከበረው ቅዳሜ መጋቢት 26 ነው። ቂጣና ወይኑ የሚዞረው ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይሆናል።