ለአሥር ዓመታት በተለያዩ ቋንቋዎች እኩል የወጡ መጽሔቶች!
ከአሥር ዓመት በፊት የስፓኒሽ መጠበቂያ ግንብ ከእንግሊዝኛው እትም ጋር በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ይዘት ኖሮት መውጣት ሲጀምር እንዴት እንደተሰማት ስትጠየቅ አንዲት ውድ ስፓኒሽ እኅት እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጥታ ነበር፦ ‘እንደተባረክን ይሰማናል፤ ምክንያቱም አሁን በእንግሊዝኛ ከሚወጣው ጋር እኩል እየተራመድን ነው። እንግሊዝኛ ስል ሁልጊዜ ትዝ የምትለኝ የይሖዋ ድርጅት ናት። ድርጅትን ስንጠራ “እማማ” እያልን ነው። በጣም የተቀራረብን እንደሆንን ይሰማናል። በጣም ደስ ይላል። ዕጹብ ድንቅ ነው!
ይህች ታማኝ እኅት በእንግሊዝኛ ሳይሆን በሌሎች ቋንቋዎች የሚወጡትን መጽሔቶች የሚያነቡትን የብዙዎቹን ስሜት ገልጻለች። ቀደም ባሉት ዓመታት በስፓኒሽ የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የሚወጡት ትምህርቶች በእንግሊዝኛ ከታተሙ ከስድስት ወር በኋላ ይወጡ ነበር። በሌሎች ቋንቋዎችም ተመሳሳይ የመዘግየት ሁኔታ ነበር። ባንድ ጊዜ ውስጥ ያንኑ ትምህርት በብዙ ቋንቋዎች ለማተም ከፍተኛ ምኞት የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው።
ስለዚህ ከሚያዝያ 1, 1984 ጀምሮ የስፓኒሽ እትም ከእንግሊዝኛው ጋር እኩል የሚወጣ የመጀመሪያው እትም ሆነ። ወዲያው በሌሎች ቋንቋዎችም እኩል መውጣት ጀመሩ። በ1985 መጀመሪያ ላይ ባንድ ጊዜ ከእንግሊዝኛው እትም ጋር እኩል የሚታተምባቸው ቋንቋዎች 23 ደረሱ። ተርጓሚዎች እየተገኙና እየሠለጠኑ ሲሄዱ በሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችም ከእንግሊዝኛው እትም ጋር እኩል መውጣት ቻሉ።
ይህ የመጠበቂያ ግንብ እትም መጽሔቱ በሌሎች ቋንቋዎች ከእንግሊዝኛው ጋር እኩል መውጣት የጀመረበት አሥረኛ ዓመት ነው። በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በ116 ቋንቋዎች የሚታተም ሲሆን 85ቱ እኩል የሚወጡ ናቸው። ይህም ማለት ከሚዘጋጁት በአማካይ 16,100,000 ከሚሆኑት የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎች መካከል 99. 3 በመቶ የሚሆኑት አንድ ዓይነት ርዕሶችና አንድ ዓይነት የሽፋን ዲዛይን አሏቸው ማለት ነው። በየሳምንቱ በሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ከሚገኙት ከ95 በመቶ የሚበልጡት ሰዎች በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት ያጠናሉ።
የመጠበቂያ ግንብ ተጓዳኝ የሆነው የንቁ! መጽሔት ከሚታተምባቸው 74 ቋንቋዎች መካከል 37ቱ በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት ይዘው ይወጣሉ። ዓመታዊው የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ በ18 ቋንቋዎች ይታተማል። በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት ይዞ የሚወጣው እንዲህ ያለው ጽሑፍ የአምላክ ሕዝቦች “በአንድ ልብና አሳብ” የተባበሩ እንዲሆኑ ያገለግላል።—1 ቆሮንቶስ 1:10