የአንባብያን ጥያቄዎች
በአምላክ ሕግ መሠረት ሥጋ ከደም ጋር መብላት የሞት ቅጣት የሚያስከትል ሆኖ ሳለ የሳኦል ወታደሮች ያልተገደሉት ለምን ነበር?
በእርግጥ እነዚህ ሰዎች አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ ጥሰዋል። ምሕረት የተደረገላቸው ግን ለደም አክብሮት ስለነበራቸው ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ከዚያ የበለጠ አክብሮት ለማሳየት ጥረት ማድረግ ይገባቸው ነበር።
እስቲ ሁኔታውን ተመልከተው። እስራኤላውያን በንጉሥ ሳኦልና በልጁ በዮናታን መሪነት ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ነበር። ‘የእስራኤልም ሰዎች’ በጦርነቱ ‘በተጨነቁ’ ጊዜ ሳኦል ሰዎቹ ጠላትን ድል ሳያደርጉ ምግብ እንዳይበሉ ያልታሰበበት የችኮላ መሐላ አማላቸው። (1 ሳሙኤል 14:24) ብዙም ሳይቆይ ይህ መሐላው ችግር ፈጠረ።
ከሳኦል ጋር የነበሩት ሰዎች ከባዱን ውጊያ ተዋግተው አሸነፉ። ሆኖም ያደረጉት አድካሚ ጥረት መጥፎ ውጤት አስከተለ። ሰዎቹ በጣም ተርበውና ደክመው ነበር። በዚህ መጥፎ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ምን አደረጉ? “ሕዝቡም ለምርኮ ሳሱ [ተስገበገቡ፤ አዓት] በጎችን በሬዎችንም ጥጆችንም ወስደው በምድር ላይ አረዱ፤ ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ።”—1 ሳሙኤል 14:32
ይህን በማድረጋቸው አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ ጣሱ። ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ለሳኦል “እነሆ፣ ሕዝቡ ከደሙ ጋር በመብላታቸው እግዚአብሔርን በደሉ” ብለው ነገሩት። (1 ሳሙኤል 14:33) አዎን፣ ሕጉ እንስሳት ታርደው የሚበሉት ደሙ ከሥጋው ተንጠፍጥፎ ከወጣ በኋላ እንደሆነ ይደነግጋል። አምላክ አንድ ቅንጣት ደም እንኳን እስከማይገኝ እንዲያንጠፈጥፉ በማዘዝ ምክንያታዊ ያልሆነ ሕግ አልሰጣቸውም። አገልጋዮቹ ደሙን በተገቢው መጠን በማፍሰስ ደም ለሚወክለው ነገር ያላቸውን አክብሮት ሊያሳዩ ይችሉ ነበር። (ዘዳግም 12:15, 16, 21–25) የእንስሳት ደም በመሠዊያ ላይ መሥዋዕት ሆኖ እንዲቀርብ እንጂ ለምግብነት እንዲያገለግል አልተፈቀደም። ሆን ብሎ ሕጉን መተላለፍ በሞት ያስቀጣ ነበር፤ ምክንያቱም የአምላክ ሕዝቦች “የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሰው ተለይቶ ይጥፋ” ተብሎ ተነግሯቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 17:10–14
የንጉሥ ሳኦል ወታደሮች የአምላክን ሕግ የጣሱት ሆን ብለው ነበርን? ስለ ደም ለተሰጠው መለኮታዊ ሕግ ምንም አክብሮት አላሳዩምን?—ከዘኁልቁ 15:30 (የ1980 ትርጉም) ጋር አወዳድር።
እንዲህ ብለን መደምደም አንችልም። ታሪኩ ‘እንስሶችን ወስደው በምድር ላይ አረዱ፤ ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ’ ይላል። ስለዚህ ደሙን ለማፍሰስ የተወሰነ ሙከራ አድርገው ነበር። (ዘዳግም 15:23) ሆኖም ደክመውና ተርበው ስለነበር የታረዱትን እንስሶች አንጠልጥለው ደሙ በሚገባ እንዲፈስስ በቂ ጊዜ አልሰጡም ነበር። በጎቹንና ከብቶቹን “በምድር ላይ” ማረዳቸው ደሙ በደንብ እንዳይፈስ አድርጎት ነበር። ከዚያም ቸኩለው የታረደው ከብት ገና ደሙ ላይ እያለ ሥጋውን መቁረጥ ጀመሩ። ስለዚህ የአምላክን ሕግ ለማክበር ቢያስቡም በትክክለኛው መንገድና በበቂ መጠን እንዲፈስ በማድረግ ሥርዓቱን አልተከተሉም።
በዚህ ምክንያት “ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ።” ይህም ኃጢአት ሆነባቸው። ሳኦል ይህን ስለተገነዘበ ትልቅ ድንጋይ አንከባልለው እንዲያመጡለት አዘዘ። ወታደሮቹንም “እያንዳንዱ ሰው በሬውንና በጉን ወደ እኔ ያቅርብ፣ በዚህም እረዱና ብሉ ከደሙም ጋር በመብላታችሁ እግዚአብሔርን አትበድሉ” ብሎ አዘዛቸው። (1 ሳሙኤል 14:33, 34) ጥፋተኞቹ ወታደሮች ሳኦል እንዳላቸው አደረጉ። “ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ።”—1 ሳሙኤል 14:35
እንስሶቹን በድንጋዩ ላይ ማረዳቸው ደሙ በበቂ መጠን እንዲፈስስ ለማድረግ ያስችላል። ሥጋው እንስሶቹ ከታረዱበት ቦታ ራቅ ተብሎ ይበላ ነበር። ሳኦል የፈሰሰውን ደም አምላክ ኃጢአተኞቹን እንዲምራቸው ለመለመን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ምሕረት ያደረገላቸው ሰዎቹ ደክመውና ተርበው የነበሩ ቢሆንም ሕጉን ለመጠበቅ በመሞከራቸው ሳይሆን አይቀርም። አምላክ ሳኦል በችኮላ የገባው መሐላ ሕዝቡ ይህን የመሰለ አሳዛኝ ድርጊት እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ እንዳደረገባቸውም ከግምት ውስጥ አስገብቶ ይሆናል።
ይህ ታሪክ አስቸኳይ ሁኔታዎች የአምላክን መለኮታዊ ሕግ ለመጣስ ሰበብ ሊሆኑ እንደማይችሉ ያሳያል። እንዲሁም ስእለት ከመሳላችን በፊት በሚገባ ልናስብበት እንደሚያስፈልገን ያሳያል። ምክንያቱም በጥድፊያ የተደረገ ስእለት በእኛም ሆነ በሌሎች ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።—መክብብ 5:4–6