የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናውን ተከተለ
የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “ፍጹም አቋሜን ጠብቄ እሄዳለሁ። አድነኝ፤ እርዳኝም” ብሎ ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 26:11 አዓት) አምላክ ፍጹም አቋሙን መጠበቅ እንዲችል ረድቶታል። የሰማያዊ አባቱን ፈቃድ በማድረጉ ይሖዋ ኢየሱስንም ባርኮታል። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናውን የተከተለውንና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቆራጥ አቋም የወሰደውን አንድ በኮሎምቢያ የሚኖር ወጣት ባርኮታል። ይህ ወጣት እንዲህ ሲል ይናገራል፦
“ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመርኩበት ጊዜ በካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ እማር ነበር። ይሁን እንጂ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚካሄደው የቅዳሴ ሥርዓት ስካፈል ኅሊናዬ ይረብሸኝ ነበር። ስለዚህ ወደ ትምህርት ቤቱ ዲሬክተር (ቄስ ነበሩ)፣ ወደ ተማሪዎች አማካሪና ወደ አለቃችን ሄድኩና በቅዳሴ ላይ ላለመገኘት እንድችል እንዲፈቅዱልኝ ጠየቅኳቸው። ፈቃዱን ባገኝም እንኳን አንዳንዶች በቅዳሴ ሥርዓቱ ላይ እንድገኝ ለማስገደድ ሞከሩ። የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ልክ እንደተጠመቅሁ ግፊቱ እየበረታ ሄደ። አባቴ ደግሞ ከትምህርት ቤት ከተባረርክ ከቤት አስወጣሃለሁ ሲል አስፈራራኝ። የእሱ ዕቅድ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ እንድማርና ሥራ እንድይዝ ነበር።
“ዲሬክተሩ ማንኛውም ተማሪ የካቶሊክ ሃይማኖት ግዴታዎችን መፈጸም ይገባዋል ሲሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀው ነበር። የዓመቱ የመጀመሪያው የቅዳሴ ሥርዓት በተከናወነበት ዕለት ቅዳሴው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ተደበቅሁ። ከዚያም ለአስተማሪው (ቄስ ናቸው) ትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር ሰጠኋቸውና የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ በቅዳሴ ሥርዓት ላይ እንደማልገኝ ነገርኳቸው። ‘ሌላ ትምህርት ቤት መፈለግ ብትጀምር ይሻልሃል’ አሉኝ። ከትምህርት ቤት ከተባረርኩ አባቴ ከቤቴ እንደሚያስወጣኝ አውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ጸለይኩና ለክፍል ጓደኞቼ በሚገባ መመሥከሬን ቀጠልኩ።
“ትምህርት ቤት ለዕረፍት ተዘጋ። የዕረፍት ጊዜ አብቅቶ ትምህርት ሲጀመር እንደገና የቅዳሴ ቀን ደረሰ። ዲሬክተሩና ሌሎቹ ቄሶች ኑዛዜዎችን ለማዳመጥ በጸሎት ቤቱ ፊት ለፊት ቆመዋል። በፍርሃት ልሸነፍ ምንም አልቀረኝም ነበር። ውስጥ ገባሁና ተቀመጥኩ። ኅሊናዬ ግን ሊያስቀምጠኝ አልቻለም። መዝሙሩ ሲጀምር ‘እዚህ ምን እሠራለሁ? አምላኬ ይሖዋ ነው። በፍርሃት ልክደው አይገባኝም። ላሳዝነው አልችልም። እርሱ ደግሞ አይተወኝም’ ብዬ አሰብኩ። ድፍረት እንዳገኝ ጸለይኩ። ከዚያም ከጸሎት ቤቱ ወጣሁና ለመናዘዝ ከተሰለፉት ጋር ቆምኩ። ዲሬክተሩ አጠገብ ስደርስ ‘መምህር፣ የመጣሁት ልናዘዝ አይደለም’ አልኳቸው። ‘እኔም ልትናዘዝ እንዳልመጣህ ገምቼ ነበር’ አሉኝ። በቅዳሴ ሥርዓቱ እንድካፈል ኅሊናዬ ስላልፈቀደልኝ በሥርዓቱ ላይ እንደማልካፈል በዚህም ምክንያት የሚመጣብኝን ሁሉ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኔን ነገርኳቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸውን ትምህርቶች የሚጻረር ነገር ለማድረግ አልችልም ነበር።
“ትክ ብለው ሲያዩኝ ቆዩና ፈገግ ብለው እንዲህ አሉኝ፦ ‘አደንቅሃለሁ። እናንተ ምሥክሮች ሁላችሁም ልትደነቁ ይገባችኋል። እናንተ ቅድሚያ የምትሰጡት ለአምላክ ነው። የመጣው ቢመጣ ሕጎቹን ከመታዘዝ ወደ ኋላ አትሉም። ግፉበት። የምታደርጉት ነገር በጣም ጥሩ ነው። ሁሉም ካቶሊኮች እንደ እናንተ ዓይነት ቅንዓትና ፍቅር ቢያሳዩ ደስ ይለኝ ነበር። ከአሁን ጀምሮ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻችን ከመሳተፍ ነፃ ነህ።’ ደስታዬ ወሰን አልነበረውም! በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናዬን ለመታዘዝ የወሰድኩትን ቁርጥ ያለ አቋም ይሖዋ ባርኮልኛል።
“በሚቀጥለው ቀን ዲሬክተሩ ተማሪዎቹን እንዲህ አሏቸው፦ ‘ሌሎች ሃይማኖቶች ቀድመውን ሄደዋል። ቅንዓት በማሳየት፣ ለአምላክ የጠለቀ ፍቅር በማንጸባረቅና ከምንም ነገር በላይ እሱን ለማገልገል በመፈለግ ለምን እንደነሱ አንሆንም? ይህ በልባችን ውስጥ ልንይዘው የሚገባ ጉዳይ ነው።’
“በመጨረሻ ዲሬክተሩ ወደ ሮም ተዛወሩ፤ አዲሱ ዲሬክተርም በሥርዓቱ ላይ አለመሳተፌን ትኩረት አልሰጡትም። አባቴም ቤቱን ለቆ ስለ ሄደ ከትምህርት ቤት እንደተመረቅኩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግቤን እዳር ማድረስ የምችልበትን አጋጣሚ አገኘሁ።”
በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናውን የተከተለውን ይህን ወጣት ይሖዋ ባርኮታል። በተመሳሳይም ፈቃዱን ለማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ ይባርካቸዋል።—ምሳሌ 3:5, 6