‘እንደ ሌሎች አትዘኑ’
ኃይለኛ ዝናብ ከወረደባት በኋላ ራሷን ዘንበል ያደረገች አበባ አይተህ ታውቃለህ? አበባዋ በጣም ታሳዝናለች። ደመናው በድንገት ዝናቡን ሲለቀው ከማንኛውም አበባ ይበልጥ ጠንካሮች የሆኑት ብዙ እንስሳትና ሰዎች እንኳን ለመጠለል ይሯሯጣሉ። አበባዋ ግን እዚያው በተተከለችበት ቦታ ሆና ዶፍ ይወርድባታል። ከዝናቡ በኋላ አበባዋ ሳትቀነጠስ ግን ራሷን ዘንበል አድርጋ ስትታይ በቀላሉ የምትጎዳ ብትመስልም ያን ሁሉ ዝናብ የተቋቋመችበት ጥንካሬ እንዳላት ታሳያለች። በአድናቆት እየተመለከትካት እያለህ ‘አበባዋ የቀድሞ ውበቷ ተመልሶላት ዳግመኛ ራሷን ቀና ታደርግ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
ሰዎችም እንዲሁ ናቸው። በነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ብዙ ዓይነት የመከራ ዶፍ ይወርድብናል። የኢኮኖሚ ችግር፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ የጤና መታወክ፣ የምንወደው ሰው ሞትና ይህን የመሰለ የመከራ ዶፍ በአንድ ወይም በሌላ ወቅት ላይ ሁላችንንም ሊያጋጥመን ይችላል። ልክ አበባዋ ከተተከለችበት ቦታ ራሷን ነቅላ ለመጠለል መሮጥ እንደማትችል ሁሉ አንዳንድ ጊዜ እኛም እነዚህን ችግሮች የምንከላከልበት መንገድ ላይኖር ይችላል። ደካሞች የሚመስሉ ግለሰቦች የሚያስደንቅ ጥንካሬ አግኝተው የደረሱባቸውን መከራዎች ተቋቁመው ማየት የአድናቆት ስሜት የሚቀሰቅስ ነው። እንዲህ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ ቁልፉ እምነት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “እምነታችሁ እንዲህ ዓይነት መከራ ሲደርስበት በውጤቱ የመጽናት ችሎታ ታዳብራላችሁ።”—ያዕቆብ 1:3 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን
ሌላው ቁልፍ ነገር ተስፋ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ የሚወደድ ሰው በሞት ሲቀጭ ቋሚዎች ተስፋ ካላቸው ሁኔታቸው በጣም የተለየ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጻፈላቸው፦ “ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።” (1 ተሰሎንቄ 4:13) በእርግጥ ክርስቲያኖች ሰው ሲሞትባቸው የሚያዝኑ ቢሆንም ከሌሎቹ ሰዎች የተለየ ሁኔታ አላቸው። ሙታን ስላሉበት ሁኔታም ይሁን ስለ ትንሣኤ ተስፋ ትክክለኛ እውቀት አላቸው።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
ይህንን ማወቃቸው ተስፋ ይሰጣቸዋል። ተስፋው ደግሞ ቀስ በቀስ ሐዘናቸውን ይቀንስላቸዋል። እንዲጸኑ ከመርዳቱም በላይ ኃይለኛ ዝናብ እንደወረደባት አበባ እነሱም ከጊዜ በኋላ ሐዘናቸው አብቅቶ ራሳቸውን ቀና ሊያደርጉና በሕይወታቸው በሚያገኙት ነገር እንደበፊቱ ሊደሰቱ ይችላሉ።